ቀጥታ፡

የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ ቁጭት ወደ ብሔራዊ ድል የሚያሸጋግር መሠረታዊ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ ቁጭት ወደ ብሔራዊ ድል የሚያሸጋግር መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ለምላሹ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የባህር በር ከንግድና ከምጣኔ ሃብት ፋይዳ ባሻገር ዓለም አቀፋዊ ትስስር፤ የጋራ ተጠቃሚነት፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችና ሌሎች ጥቅሞችን ማረጋገጥ የሚቻልበት ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑ ይታወቃል።

ኢኮኖሚዋ በማንሰራራት ላይ የሚገኘውና በአፍሪካ ሁለተኛውን የህዝብ ቁጥር የያዘችውን ኢትዮጵያን ለባህር የቅርብ ሩቅ አድርጎ መዝለቅ የማይቻልና የህልውና ጉዳይ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያጣችው የባህር በር የሚያስቆጭ እና ምላሽ የሚገባው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህን ከታሪካዊ ቁጭት ወደ ብሔራዊ ድል የሚወስደውን የባህር በር ጥያቄ ከዳር ለማድረስ ሁሉም በጋራ መስራትና መረባረብ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

የህዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሱራፌል እሸቱ (ኢ/ር) እንደገለጹት፤ ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገርን መምራት በሚል ሽፋን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ግብ አንግቦ ሲሰራ ቆይቷል።

ቡድኑ ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያለአግባብ እንድታጣ በማድረግ፣ ከኢትዮጵያውያን አዕምሮ የማይወጣና ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ክህደት መፈጸሙን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ዜጎች ስለ ባህር በር ምንም ዓይነት ሃሳብ እንዳይሰጡ ገደብ በመጣል፣ ትውልዱ ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት እውቀት እንዳይኖረው በማድረግ አምባገነናዊነቱንና ለብሔራዊ ጥቅም ግድ የሌለው መሆኑን በተግባር ማሳየቱን አስታውቀዋል።

ለዚህም የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ትልቅ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ የባህር በር ጉዳይ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሌሎችም አካላት የጋራ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ ፓርቲያቸው ከመንግስት ጎን ሆኖ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አርክቴክት ዮሃንሰ መኩሪያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክአ-ምድራዊ አቀማመጥ፣ በሕዝብ ቁጥር እንዲሁም በሕጋዊ መስፈርት የባሕር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት ግልጽ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ያነሱት አርክቴክት ዮሐንስ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለውና ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑን አብራርተዋል።

የመደመር መንግሥት ሀገሪቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የባሕር በር ጉዳይ ዋና አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ፣ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ተግቶ እየሠራ ነውም ብለዋል።

ይህም ኢትዮጵያውያን በግፍ የተነጠቁትን የባሕር በር በማስመለስ ለዓመታት የቆየውን ቁጭት ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በዓድዋ እና በሕዳሴ ግድብ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ልዩነቶቻቸውን በመተው ለባሕር በር ጥያቄ ስኬት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አበራ በቀለ ናቸው።

ታሪካዊ ጠላቶች በሴራ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንድታጣ ማድረጋቸው ትክክል እንዳልነበር መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሀገራት ጭምር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተው፤ ጥያቄው የሁሉም ፓርቲዎች የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም