ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ጀመረች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ጀመረች
ኢትዮጵያ በነዳጅ ምርቶች ላይ ያላትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ለመቀነስ እና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂዋን ለማሳካት በሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ወደመጠቀም የመሸጋገር ሰፊ ሀገራዊ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።
ይህ ስትራቴጂ ሀገሪቱ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት በስፋት ለመጠቀምና የትራንስፖርት ዘርፉን ዘላቂና ወጪ ቆጣቢ በሆነ የኃይል አማራጭ ለማዘመን የያዘችውን የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ራዕይ የሚያሳካ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ የተገነባውን የመጀመሪያው ምዕራፍ የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት በይፋ በመረቁበት ወቅት ሀገሪቱ በራሷ አቅም የምታመርተውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ገበያ በማውጣት ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ለአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ማዋል እንደሚጀመርና ይህም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሮ ተጨማሪ ብስራት መሆኑን ገልጸው ነበር።
ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ወደ መሬት ለማውረድም ባለፉት ወራት በርካታ የተቀናጁ የሎጂስቲክስ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ከእነዚህም መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ከሚመረትበት ስፍራ ወደ አዲስ አበባ የማጓጓዝ፣ ልዩ የጋዝ ማደያ ጣቢያዎችን የመገንባት እና ነባር ተሽከርካሪዎችን ወደ ጋዝ ቴክኖሎጂ ለመቀየር የሚያስችሉ ሰፊ የቅድመ-ዝግጅትና የመሠረተ ልማት ስራዎች በስፋት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
እነዚህ ሰፊ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ፣ ይህን ሀገራዊ ራዕይ በተግባር ያረጋገጡት የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጥ ስራ ተጠናቆ ዛሬ በይፋ ሥራ ላይ መዋላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብስረዋል።
በነዳጅ አገልግሎትር የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎችና መሐንዲሶች በራስ አቅም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጡ ተግባር ደግሞ የሀገር ውስጥ አቅምንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በተግባር የተጀመረው ይህ ስራ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ከፍታ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 400 የሚደርሱ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ የከተማ አውቶብሶች ወደ ሀገር ቤት እንደሚገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።