ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማእከል ብልሹ አሰራርን በመቅረፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው

ጎንደር፣ ጥቅምት 20/2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተጀመረው መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና ብልሹ አሰራርን በመቅረፍ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን  የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማውን በጎንደር ከተማ አካሒዷል።


 

የቢሮው ኃላፊ ባንቺአምላክ ገብረማርያም በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘው የሪፎርም ትግበራ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና የህብረተሰቡን ችግርለመቅረፍ እያስቻለ ነው።

በዚህም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን  ዲጅታላይዝ በማድረግ በዘርፉ የላቀ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።


 

በተለይም መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ህዝቡ በአንድ ቦታ በተደራጀ ሁኔታ ፈጣን፣ ግልጽና ፍትሃዊ  አገልግሎት የሚያገኝበትን እድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

ይህም የአገልግሎት ሰጭ ባለሙያዎችን ስነ ምግባር በማሻሻል በህብረተሰቡ ዘንድ የአገልግሎት እርካታ መፍጠር መቻሉንም አስገንዝበዋል። 


 

የጎንደር ከተማ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነፃነት መንግስቴ በበኩላቸው ሙያተኞችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማላመድ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል።

ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ታች ድረስ ለማድረስ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።

"ባለሙያዎችን በበቂ እውቀት፣ ክህሎትና በስነ-ምግባር በማነጽ ህብረተሰቡን በብቃት እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ  የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ ሳልህ ኑር ሁሴን ናቸው። 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የጎንደር ቀጠና የዘርፉ መምሪያ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም