ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ሚና እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ሚና እየተወጣች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ ኮንግ ገለጹ።

12ኛው የጣና ፎረም "በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በውቢቷ ባሕር ዳር ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአሁንና የቀድሞ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጭዎች በጣና ፎረም ላይ ታድመዋል፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ያላትን አበርክቶም አድንቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ ኮንግ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጣና ፎረም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በአፍሪካ ችግሮች ላይ የሚወያዩበት ትልቅ መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ጣና ፎረም ያለውን አህጉራዊ ጠቀሜታ ያለው የሰላምና ደህንነት መድረክ ማዘጋጀቷ ትልቅ ምሥጋናና ክብር ይገባታል ብለዋል።

ጣና ፎረም አፍሪካውያን በቀጣናው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ተሰባስበው መልዕክታቸውን የሚያጋሩበት መድረክ መፍጠሩንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራትና ተቋማት ለቀጣናውና ሰላም በሚበጁ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለችግሮቹ የመፍቻ ቁልፍ መቅረፅ አለባቸው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ የስምምነት አጀንዳዎችን አቅርቦ በማደራደር ለቀጣናው ሰላም ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ግጭት የማቆም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ በንግግር እንዲፈቱ ገንቢ ሚና ተወጥታለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ህዝብ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና የምትወጣ መልህቅ መሆኗን ገልጸዋል።

ሀገራት የባህር በር ጥያቄያቸው የሚረጋገጥበት ዓለም አቀፍ ህግ እንዳለ የገለጹት ልዩ መልዕክተኛው፤ ኢትዮጵያም በሰላማዊ መንገድ በውይይት ማግኘት አለባት ብለዋል።

በቀጣናው ያለው ውጥረት መርገብ አለበት ያሉት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጉዋንግ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በሰላማዊ ውይይት እንዲቋጭ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

✍️ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ

#የመደመር_መንግሥት

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም