ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የኢንዱስትሪ ሰላምንና የሠራተኞችን ደህንነት በማረጋገጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

ባህር ዳር፣ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ):-በባህር ዳር ከተማ የኢንዱስትሪ ሰላምን እና የሠራተኞችን ደህንነት በማረጋገጥ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።

በኢንዱስትሪዎች የሥራ ላይ አደጋ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አተገባበር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጎሹ እንዳለማው በመድረኩ እንደገለጹት፤ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት የጎደለው ስምሪት እየተሰጠ እንደሚገኝ በምልከታ ተረጋግጧል።

ይህን ህግ ያልተከተለ አሰራር መስተካከል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለሠራተኞች የደህንነት አልባሳትና ጫማዎችን ማቅረብ የኢንዱስትሪውን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ለምርታማነት ማደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በከተማዋ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ከ300 በላይ ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደማምረት ሥራ እንደገቡ አስታውሰው፣ ከ700 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ የኢንዱስትሪዎች ግንባታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፣ በክልሉ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በተጨማሪም የግንባታ ቦታ ተረክበው በሚፈለገው ፍጥነት ወደተግባር ያልገቡ ባለሃብቶችን በመደገፍ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥ በላቀ ቅንጅትና ትብብር መስራት ያስፈልጋል።

ሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ተደራጅተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልፀው፤ ይህን የመደራጀት መብት የሚከለክሉ አሠሪዎች ላይ ቢሮው ጥብቅ እርምጃ ይወሳዳል ብለዋል።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ለሠራተኞች ነጻ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች የሠራተኛውን መብት ከማክበር ባለፈ የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ ቁሶችን ሊያሟሉ ይገባል።

መንግስት መሬት በማቅረብ የኢንዱስትሪውን ችግር እየፈታ መሆኑን አስታውሰው፣ አሰሪና ሠራተኛው ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ ምርታማነትን ለማሳደግ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም