ቀጥታ፡

የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ- ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)

ሆሳዕና ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

የክልሉ የከተማና የኢኮኖሚ ዘርፍ ምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ።

ከተሞችን በኮሪደር ልማት ምቹና ሳቢ ከማድረግ በተጨማሪ ለኢንቨስትመንት ተመራጭነታቸውን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህዝቡን  የልማት ጥያቄ የመመለስ ፣ የዋጋ ንረትን የመከላከል ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ተኪ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ዜጎችን በስራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው የመደመር መንግሥት በኮሪደር ልማት ፅዱ ፣ ውብና ማራኪ ከተሞች እንዲፈጠሩ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዚህም በክልሉ  በመጀመሪያው ምዕራፍ 74 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማትና 10 ሄክታር የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።

የከተሞችን እድገት በማፋጠን የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ዉጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሰው በዘርፉ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በመድረኩ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ጨምሮ የክልል ፣ የዞን ፣ የልዩ ወረዳ ፣  የወረዳና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም