ኢትዮጵያ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅሟን በተግባር እያረጋገጠች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅሟን በተግባር እያረጋገጠች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅሟን በተግባር እያረጋገጠች መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን 7ኛው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክተር ነኢማ ዘይኑ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ መዋቅራዊ ሥራዎችን እያከናወነች ነው።
በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸው ብዙ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አውድ የጤና ቱሪዝም ሥርዓትን በመዘርጋት ዘርፈ ብዙ አቅሞችን እየገነባች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ጉባኤው ጥቅምት 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጸው ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍትና ሀገራት በድንገተኛ ሕክምና ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ በጤና ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸው በነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሰለጠኑ፣ በቂ መሣሪያ የተሟላላቸው በተቀናጀ መንገድ የሚሠሩና በተገቢው ሰዓት የሚደርሱ የሕክምና ቡድኖች ሕይወትን ለማዳን ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አቅሟን በተግባር ለማረጋገጥ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰዷን አንስተዋል።
በዚህም በ2018 ዓ.ም የአደጋ ሕክምና ድጋፍ ቡድን Disaster Medical Assistance Team (DMAT) ማቋቋሟን ገልጸዋል።
ይህም ሀገራዊ የቅንጅት እና የሥራ አፈጻጸም ሥርዓቶች በመሬት ላይ ለመፈተሽ እና ጠንካራ የዝግጁነት አቅም ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በ 2019 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በማቋቋም የዓለም ጤና ድርጅት ጥብቅ የማረጋገጫ ሂደት በማጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ምደባ ማግኘቷን ተናግረዋል።
የድንገተኛ አደጋ ሲከሰት በውጤታማነት ምላሽ ለመስጠት የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ዘመናዊ ሥርዓቶች፣ የተሟሉ መሣሪያዎች እና የላቀ የቅንጅት ሥራዎች እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
ለዚህም ስኬት የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች የስትራቴጂክ ዕቅድ (2025 – 2030) እንደ ዋና መመሪያ ሆኖ መቀረጹን ተናግረዋል።
ከዓለም አቀፉ ጉባኤ አስቀድሞ ጥቅምት 23 ቀን 2019 ዓ.ም ሰፊ የሙከራ ልምምድ (Simulation Exercise - SIMEX) እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ትብብር፣ የእርስ በርስ መማማር ከአቅም በላይ የሆኑ ቀውሶች ሲከሰቱ የጠንካራ ብሔራዊ አቅም የምላሽ ሥርዓቱ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችል አስገንዝበዋል
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የድንገተኛ አደጋ ፕሮግራም ኃላፊ ፕሮፌሰር ዳሪኖ ቫልዴ በበኩላቸው የድንገተኛ አደጋ የሕክምና ቡድን ከፍተኛ ሥልጠና የወሰዱ የሙያ ባለሙያዎች ቡድን መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ ከጤና ተቋማት ውጭ ሕክምና ለመስጠት የሕክምና ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶች እና ሎጅስቲክስ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤው በርካታ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት እና የአደጋ ጊዜ የሕክምና ምላሽን ለማጠናከር የሚያስፈልጉ ተግባራዊ ቃል ኪዳኖች የሚፈጸሙበት ጤና ባለሙያዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በአስቸኳይ የሕክምና ምላሽ ቡድኖች ልማት ረገድ በአብነት የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለዚህ ዕውቅና መስጠቱን ገልጸው ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።