ለሕዝቡ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዝቡ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራት ተከናውነዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ለሕዝቡ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ተዳራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያዎቹን 26 ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተለወጡ አውቶብሶች ሥራ አስጀምረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች ዘመኑን በዋጀ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽነታቸውን ባረጋገጠ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም አዳዲስ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን በመግዛት ማቅረብ መቻሉን በአብነት ጠቅሰዋል።
ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ለመጀመሪያ ጊዜ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ጋዝ የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት አቅም መፍጠራችን የአየር ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።
መንግሥት የማኅበረሰቡን የትራንስፖርት ጫና ለማቃለልና የከተማ አውቶብስ ትራንስፖርትን ለማቀላጠፍ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ ነዋሪዎች ዝቅተኛ ክፍያ እንዲከፍሉ እየሠራ ቢሆንም፣ አሁንም የአገልግሎቱ ተደራሽነት ዋና ማነቆ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ይህን ጫና ከማቃለል አንጻር በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶችን ተደራሽ ማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
ሕዝቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ከንቲባዋ አንበሳ አውቶብሶችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የማሸጋገር ሥራ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያዎቹን 26 ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተለወጡ አውቶብሶች ወደ ሥራ ባስገቡበት ወቅት፣ ሀገሪቱ በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እና ሀገር ውስጥ እየተመረተ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶብሶች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።