ኢትዮጵያ መሻትና ፍላጎቷን በተባበረ ፍጥነት ማሳካት መለያ መታወቂያዋ እያደረገች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መሻትና ፍላጎቷን በተባበረ ፍጥነት ማሳካት መለያ መታወቂያዋ እያደረገች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ መሻትና ፍላጎቷን በተባበረ ፍጥነት ማሳካት መለያ መታወቂያዋ እያደረገች ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ በነዳጅ ይሰሩ የነበሩ የመጀመሪያዎቹን 26 የከተማ አውቶብሶች ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ሥራ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የትራንስፖርትና የቤት ዋጋ ነው ከፍተኛው።
ለዚህም የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የቤት ጥያቄዎች በተጀመረው ስኬታማ ጉዞ እየተፈቱ ሲሄዱ ሰዎች ባላቸው ገቢ ልክ የተሻለ ለመኖር የሚያስችል ዕድል እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
የጋዝ ምርትን ወደ ውጤት የመቀየር ሂደት ለመንግሥት በጣም ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመናገር ባሻገር ለህዝብ ጥቅም ማዋልም የአንድ መንግሥት መለኪያ መሆኑን አንስተዋል።
እኛ የምንታወቀው በመጀመር ሳይሆን ፕሮጀክትን በጥራትና በፍጥነት መጨረስ ላይ ነው፤ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ፈጽመን ማሳየት ነው፤ የምንናገረውን ወደ ተግባር መቀየር ነው፤ ይኸም መለያ መታወቂያችን ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ባሻገርም በአፍሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት መለያ የሚናገረውን ይፈጽማል የሚል እሳቤ እየጎላ መምጣቱን አብራርተዋል።
የሕዝብ መሻት በጣም ብዙ ስለሆነም ጥራትን ከፍጥነት ጋር ያነጻጸረ አፈጻጸምን በመከተል የዜጎችን የሕይወት ጫና በማቃለል የሚጨበጥ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የእኛ ፍላጎት ምግብን በበቂ ደረጃ አምርቶ ራስን መመገብ፣ የትራንስፖርት ሥርዓቱን ወደ እኛ አቅም መቀየር፣ ሀገር ውስጥ ያሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ግብዓት በመጠቀም ዋጋቸውን መቀነስ ነው ብለዋል።
የሞጆና የደብረ ብርሃን የሴራሚክስ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያን ፍላጎት መቶ በመቶ እንደሚያሟሉ በመጠቆም፤ እስከ ቅርብ ጊዜም የፊዩል ነዳጅ እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሁለቱንም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ በመቀየር ለፋብሪካዎቹ ተብሎ የሚገባውን ናፍጣ በማስቀረት በጋዝ ባነሰ ዋጋም ስለሚያመርቱ ሴራሚክሱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ እንደሚደርስ አንስተዋል።
ይህም በሚገነባው ቤት ላይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ 100 የሚጠጉ የሴራሚክ ማጓጓዣ መኪኖች ወደ ሀገር ቤት እንደሚገቡ አስታውቀዋል።
ከፋብሪካ ወደሚሰራው ቤት መጓጓዣውም ሆነ የሴራሚክ ምርቱ ዋጋው ያነሰ፣ ቤት በማምረትም ሆነ ምግብን ከገጠር ወደ ከተማ በማምጣትም በከተማ ያለ እንቅስቃሴ ላይም የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል አንስተዋል።
ይህም ግሽበትን በመቆጣጠር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የውጭ ምንዛሬ ወጪ ፍላጎት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን መልካም ጅምር ማወቅ አለበት፤ መልካም ጅምርም ፍጻሜ አይደለም፤ የተፈጥሮ ጋዝ መጀመራችን አስደሳች ነገር ነው፤ ያንንም ወደ ተጠቃሚና ፋብሪካ ግብዓት ማድረስ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፤ መስፋትም አለበት ብለዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት ምዕራፍ ሁለት መጀመሩን በመጠቆም፤ ይኸ ሲደርስም ለማዳበሪያ ግብዓት ይሆናል፣ ለኃይል ግብዓት ይሆናል፣ ኃይልም ይመረትበታል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያውያን መልካም ጅምሮችን በማላቅ አጋርና ተባባሪነቱን በማስቀጠል የኢትዮጵያ ተስፋ በብዙ መንገድ እየታየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በልማቷ በጣም አመርቂ ውጤቶች እየታዩ ነው፤ በሰላሟም ለውጦች አሉ ብለዋል።
ይህንን አጠናክሮና አስፍቶ መስራት ልጆቻችን የተሻለ ሀገር ይኖራቸዋል፤ ሀገር በአንድ ጀምበርም ሆነ በአንድ ትውልድ አትገነባም፤ ሀገር መገንባትም ውስብስብ ሂደት እንዳለው አስገንዝበዋል።
የተለያየውን ሀገር መገንቢያ ምሰሶዎች እኩል በማሳደግ እኩል መገንባትና እኩል መጠበቅ እንደሚፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሕግ ማስከበር ሥራ ሲሰራ ልማት ከቀረ፣ ልማት ሲሰራም የዜጎችን ሕይወት የማይለውጥ ከሆነ አብሮ አይሄድም ብለዋል።
ይህንን አስተሳስሮ ለመሄድም የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡሶች ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚነት የመቀየር ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ጎዴ ያየነው አዲስ አበባ ላይ ስላየን፤ አዲስ አበባ ያየነው ደግሞ በዜጎቻችን ሕይወት ነገ ስለምናየው ደስ ብሎኛል፤ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠይቀናል፤ የዜጎቻችንን ሕይወት ማቅለል ይኖርብናል ብለዋል።
ዜጎቻችንም ይህንን ተስፋ እያዩ የሰው ልጅ መኖሪያና ሕይወት ማስቀጠያ መንገድ ተስፋ ነው፤ ተስፋን እያዩና ብሩህ ነገር እያዩና እያሰቡ በትጋት መስራት እንደሚጠቅባቸው አስገንዝበዋል።
ይህ ጊዜ በኢትዮጵያ ለልጆቻችን በጣም በጣም ተስፋ ሰጪ እና ብሩህ ነው፤ በርትተን እንስራ። ከጥረት፣ ከስራ፣ ከድካሞች የሚገኙት የተሻሉ ውጤቶች የሚታዩት በልፋት ብቻ ነው ብለዋል።
ሀገር የምንቀይረው በጋራ ጥረት፣ ስንደመር ብዙ ጉልበት፣ ብዙ አቅም፣ ብዙ እውቀት፣ ብዙ ሀብት ይሰበሰባል፤ ያንን ለሀገር ግንባታ እናውለዋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተስፋ አላት፤ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ትጸናለች፤ መሻቶቿም ፍላጎቶቿም በተባበረ ፍጥነት ታሳካለች ሲሉም አስገንዝበዋል።