ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 400 የሚደርሱ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ አውቶብሶች ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 400 የሚደርሱ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ የከተማ አውቶብሶች ወደ ሀገር ቤት እንደሚገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ በነዳጅ ይሰሩ የነበሩ የመጀመሪያዎቹን 26 የከተማ አውቶብሶች ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ሥራ አስጀምረዋል።


 

በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፤ ከጥቂት ወራት በፊት ጎዴ የሚገኘው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት መበሰሩን አስታውሰዋል። 

የጎዴ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ውጤትም ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ ላለፉት ወራት ሰፋፊ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስረድተዋል። 

የተፈጥሮ ጋዝ እና ፈሳሽ ጋዝ ባሕሪያቸው ይለያያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ከጎዴ የጋዝ ምርትን በማጓጓዝ ለየት ያለ ማከማቻና ማደያዎችን የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን አንስተዋል። 

እስካሁን በቤንዚንና ናፍጣ ይሰሩ የነበሩ አውቶቡሶችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መቀየርም ተጨማሪ ሥራ በመሆኑ፤ ኢንጂኖችን ከተለያዩ ሀገራት በማስመጣት የአዲስ አበባ ከተማ 26 የከተማ አውቶቡሶችን ለጋዝ ምቹ የማድረግ ሥራ መሰራቱን አንስተዋል። 


 

በዚህ መንገድ ከሄድን ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ 400 በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ የከተማ አውቶቡሶች ታዘዋል፤ በሚቀጥሉት ሦስት ወራትም ይገባሉ ብለዋል። 

ጎን ለጎንም በቤንዚንና ናፍጣ የሚሰሩ አውቶቡሶችን ኢንጂን በመቀየር ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 

ይህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ያለውን የናፍጣ ተጠቃሚ አውቶቡስ ሙሉ በሙሉ ወደ ጋዝ እንድንቀይር ያስችለናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም