ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር በጋራ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች- ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢንተርፖል ጋር በጋራ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች- ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ከዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር /ኢንተርፖል/ ጋር በጋራ መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የዓለም አቀፍ የፖሊስ ሕብረት ድርጅት /ኢንተርፖል/ ዋና ፀሐፊ ቫልደሲ ኡርኪዛ እና የልዑካን ቡድናቸው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢንተርፖል አባል ሀገራት የሕግ አስከባሪዎች ደረጃውን የጠበቀና ከፍተኛ ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ከሚታወቀው የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ጋር የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ተፈራርሟል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ሕብረት አባል ሆኗል።
የኢንተርፖል ዋና ጸሀፊ ቫልደሲ ኡርኪዛ ኢንተርፖል ለኢትዮጵያ በሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ሚናቸው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ኢንተርፖል ትርጉም ያለው ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ በማንሳት፤ ትብብሩን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ሕብረትን መቀላቀሉን የሚያበስር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን ገልጸዋል።
ይሄውም የኢትዮጵያ ፖሊስን የስልጠናና ተቋማዊ ዕድገት በማሻሻል የፖሊስ ሠራዊቱን የትምህርት ደረጃ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የተላበሰ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኢንተርፖል አባል ከሆነችበት እኤአ 1958 ጀምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል፣ የወንጀል መረጃ እና በአቅም ግንባታ የላቀ ትብብር እንዳላት ገልጸዋል።
የወንጀል መረቦች እየጨመሩ በመጡበት ዘመን ማንም ሀገር ብቻውን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል አይችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ይሄንን በመረዳት በመረጃ ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂና በጋራ ዘመቻ ትብብሩን ማጠናከር እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በሰላም የምታከናውን መሆኗን ገልጸው፤ በቀጣይም የኢንተርፖል አፍሪካ 2027 ኮንፍረንስ፣ የ2028 የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባኤ እና ኮፕ 32 ታዘጋጃለች ብለዋል።
እነዚህ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ኢትዮጵያ ያላትን ተቋማዊ አቅምና ዓለም አቀፋዊ ትብብር የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ለዓለም አቀፍ ፖሊስ ትብብር፣ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።
የኢንተርፖል ዋና ጸሀፊ ቫልደሲ ኡርኪዛ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል ረገድ ከአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪ ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ጋር በመስራታችን እንኮራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ሕብረት በመቀላቀሉ ደስ ብሎናል ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ በአፍሪካ የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል ሕብረቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ሕብረትን መቀላቀሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናውን የተሳለጠ ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላትን ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ይፈጥራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የሚቀርጸው ስርዓተ ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት እንደሚኖረው ገልጸዋል።