የመደመር መንግሥት የሕዝብ አገልግሎትን በማዘመን የተሰጠውን የሕዝብ ሀላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የሕዝብ አገልግሎትን በማዘመን የተሰጠውን የሕዝብ ሀላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን፣ በማቀላጠፍና የአገሪቱን የረጅም ጊዜ የልማት ግብ እውን በማድረግ የተሰጠውን የሕዝብ ሀላፊነት በቁርጠኝነት እየተወጣ ይገኛል ሲሉ የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ኸይረዲን ገለጹ።
የመሶብ አገልግሎት የሩብ ዓመት አፈጻጸም ዙሪያ ከማዕከላት ኃላፊዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል ብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ኸይረዲን፣ የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ፣ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መሶብ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ኸይረዲን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ከሕዝብ የተቀበለውን ኃላፊነት አገልግሎትን በማዘመንና በማቀላጠፍ ከግራንድ ስትራቴጂው ጋር አጣጥሞ እየተገበረ ይገኛል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም፣ የመደመር መንግሥት ቀዳሚ ግብ የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው፣ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የመሶብ አንድ ማዕከላት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ዓለም አቀፍ የISO (አይኤስኦ) ሰርቲፊኬሽን ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት መሠረት በማድረግ፣ የመሶብ አገልግሎት ማዕከላትን በክልሉ በፍጥነት ለማስጀመር ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።