የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦7ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከጥቅምት 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን 7ኛው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክተር ነኢማ ዘይኑ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ መዋቅራዊ ስራዎችን እያከናወነች ነው። በዚህም በጤናው ዘርፍ ብዙ አቅም መገንባቷን ተናግረዋል።
ጉባኤው ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸው፤ ሀገራት በድንገተኛ ሕክምና ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋ በጤና ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል።
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱን ጠቁመዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የድንገተኛ አደጋ ፕሮግራም ኃላፊ ፕሮፌሰር ዳሪኖ ቫልዴ በበኩላቸው፤ ጉባኤው በርካታ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው የድንገተኛ አደጋ ጤና ባለሙያዎች እርስ በእርስ የሚማማሩበት መድረክ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በድንገተኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።