ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የህክምና ምርቶች ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የህክምና ምርቶች ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው ሲሉ የሄልዝ ፎር ዲቭሎፕመንት ድርጅት መሥራችና ሀላፊ ዶክተር ኢየን ባርተን ገለጹ።                 

ዶክተር ኢየን ባርተን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ኢትዮጵያ መድሃኒትን ጨምሮ የህክምና ምርቶች ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ውጤታማ ጉዞ ጀምራለች።   

በመድሃኒት አቅርቦት ዘርፍ በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት መስራታቸውን የገለጹት ሀላፊው፤ ከሪፎርሙ በፊት የነበረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረትና የአሰራር ጉዳዮች ሥራውን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ያነሳሉ።       

ሆኖም የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለመለወጥ መንግሥት የወሰደው ቁርጠኛ አቋም ለባለኃብቶች አዳዲስ ዕድሎችን የከፈተ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።    

በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እና በንግድ ባለቤትነት ዙሪያ በመንግሥት የተመሩ ማሻሻያዎች ኢንቨስተሮችን እየሳቡ መሆኑን ተናግረዋል።  

በኢትዮጵያ የተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የሚደነቅ ነው፤ሌሎች ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም እመክራለሁ ሲሉም ገልጸዋል።   

በአፍሪካ መድኃኒቶችን፣ ክትባቶችን እና የሕክምና መሣሪያዎችን በራስ አቅም ለማሟላት አህጉራዊ ጥረት መጀመሩን የጠቀሱት ዶክተር ኢየን በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ እርምጃ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።       

የኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር እና እያደገ ያለው የኢኮኖሚ አቅም በአፍሪካ ደረጃ ሥራቸውን ማስፋፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ተመራጭ መዳረሻ እንደሚያደርጋትም አብራርተዋል።         


 

የአፍሪካ በህክምና ምርቶች ራስን የመቻል ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለም በማለት፤በመስኩ ውጤታማ ለመሆን የሰው ኃይል፣የኢኮኖሚ ኃብትንና የሀገር ውስጥ የምርት አቅምን በተሻለ መንገድ መጠቀም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።        

ለዚህም ያለንን ችሎታ፣አቅምና የገበያ አቅሞቻችን መመርመር ይገባናል ያሉት ዶክተር ኢየን  ለምናገለግላቸው ታካሚዎች የገባነውን ቃል በተግባር ለመፈጸም መትጋት ይገባናል ብለዋል።  

በአፍሪካ በህክምና ምርቶች አቅርቦት ላይ ውጤታማ ለመሆን ሰፊ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል። 

መንግሥታት በመስኩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በምርምርና ልማት፣ በፈጠራ ማዕከላት እንዲሁም በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ይበልጥ ሊያሳድጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም