ቀጥታ፡

በአዲስ ቤት ዘመናዊ ኑሮና አዲስ ህይወት መኖር ጀምረናል - አርሶ አደሮች

ነቀምቴ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ በአዲስ ቤት ዘመናዊና አዲስ ህይወት መኖር ጀምረናል ሲሉ በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የጉቶ ጊዳ ወረዳ 'መደ ጃለላ' ሞዴል መንደር የሚኖሩ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የገጠሩን ህብረተሰብ ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር ባለፉት ዓመታት የተቀናጀ «የሞዴል መንደሮች ግንባታ» ሀገራዊ ኢንሼቲቭ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል።


 

በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳም የተገነቡ የሞዴል አርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች የአካባቢውን አርሶ አደሮች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት በላቀ ደረጃ በመቀየር ላይ ናቸው።

አዲስ የመኖሪያ ቤት ከተገነባላቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ጉርሜሳ ቦንጋ እንደገለጹት፤ አዲሱ የመኖሪያ ቤት ቀደም ሲል የነበረባቸውን እንግልትና ጫና በማቃለል ትልቅ እፎይታ ፈጥሮላቸዋል።


 

ቀደም ሲል የነበረውን ከብቶችና ሰዎች በአንድ ጣሪያ ሥር የመኖር ልምድ በመለወጥ፣ የእንስሳት መኖሪያ ከሰው መኖሪያ ቤት ተለይቶና ጽዳቱ ተጠብቆ በመዘጋጀቱ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ማሻሻሉን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የመደ ጃለላ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ለበታ በበኩላቸው፤ መንግሥት የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማካሄድ ብቻ ሳይወሰን የአኗኗር ዘይቤያቸውን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር አቅጣጫ ማስያዙን ተናግረዋል።


 

አክለውም በግቢያቸው ውስጥ ማር፣ እንቁላል፣ ወተትና የፍራፍሬ ምርቶችን በማምረት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውንና ይህም የአኗኗር ዘይቤያቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳሻሻለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በባዮጋዝ ኃይል ምግብ ማብሰል በመጀመራቸው ከጪስና ከከባድ ድካም መገላገላቸውን የገለጹት ነዋሪዋ፤ ተማሪ ልጆቻቸውም የመብራት አቅርቦት በማግኘታቸው በምቾት ማጥናታቸው በትምህርት ውጤታቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ዮሴፍ ጌታቸው በበኩላቸው፤ መንግሥት የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት ለመቀየር እንዲህ ዓይነቱን ዘመናዊ የልማት ውሳኔ በማሳለፉና በመተግበሩ አመስግነው፣ በውጤቱም ዘመነኛና ዘላቂ ለውጥ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

አዲሱ የመኖሪያ ቤት ከሙሉ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ጋር መሰጠቱ ኑሯቸውን በእጅጉ እንዳቀለለውና የእንስሳት መኖሪያው ተለይቶ መሰራቱም ጤናቸውን ለመጠበቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።

መንግሥት የገጠሩን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የጀመረው የሞዴል መንደሮች ግንባታና የአርሶ አደሩን መኖሪያ ቤቶች ምቹና ጽዱ አድርጎ የማደራጀት ሥራ በወረዳው በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የጉቶ ጊዳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ቡልቻ ናቸው።


 

የአርሶ አደሩን የመኖሪያ ቤት በማዘመን የተጀመረውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ መነሻ በማድረግ በወረዳው ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻሉም በላይ ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ አካባቢ በመፍጠር የቤተሰብን ሕይወት ለማደስ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም