ቀጥታ፡

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተመዘገበው ስኬት ለቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ሚና እያበረከተ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና በተፋሰስ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለቀጣናው የጋራ እድገትና ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሦስተኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት "ለውሃና ኢነርጂ ዋስትና የተጠበቀለት የወደፊት ሁኔታ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸውን ፖሊሲዎችና አጋርነቶችን ማሳደግ" በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች መካሄዱን ቀጥሏል።


 

በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ሚካኤል መሀሪ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የውኃ ሀብትን በተቀናጀ አስተዳደር ማልማት የውኃ፣ የምግብና የኢነርጂ ደህንነትን በአንድነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸውን የውኃ ማከማቻና መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት የመስኖ ልማትንና የኤሌክትሪክ ኃይል ምርትን በተቀናጀ መንገድ ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አባይ ወንዝ ሥርዓት ከሚገባው ውኃ ከ86 በመቶ በላይ የምታበረክት መሆኗን አንስተው፣ የውኃ ሀብቷን በአግባቡ ማልማትና መጠበቅ ለሀገር ውስጥ ልማት ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ጥቅምም አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ በተፋሰስ ልማትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ እያከናወነች ያለችውን በርካታ ሥራዎች አንስተው፤ የላይኛው ተፋሰስ ሥነ-ምህዳርን መጠበቅ ለሀገር ውስጥ ልማት እንዲሁም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ጥቅም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በወንዞች ድንበር ተሻጋሪ አስተዳደር ላይ በጋራ ጥቅምና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውኃና ኢነርጂ ዘርፎች የሚደረጉ ፖሊሲዎችና የልማት ውሳኔዎች በሳይንሳዊ ጥናትና በተጨባጭ መረጃ ላይ መመሥረት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን ማሳደግ፣ የአገር ውስጥ ተቋራጮችንና የግሉን ዘርፍ አቅም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የውኃ፣ የኢነርጂ፣ የምግብና የሥነ-ምህዳር ትስስርን በጋራ ማየት ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የዘርፎቹ ጉዳይ ከቴክኒካዊ ውይይት ባለፈ ከሀገራዊ ህልውና፣ ብልጽግናና ሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በውኃና ኢነርጂ ሳምንት በአረንጓዴ ኢነርጂ፣ በኤሌክትሪክ ተደራሽነት፣ ጤናንና አካባቢን የሚጠብቁ የማብሰያ ኃይል አማራጮችን በማስፋፋት፣ በተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር፣ በንጽህናና በዲጂታል ፈጠራ ዙሪያ ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም