የቡና ምርታችንን በጥራት በመሰብሰብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠራን ነው- የካፋ ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ምርታችንን በጥራት በመሰብሰብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠራን ነው- የካፋ ዞን አርሶ አደሮች
ቦንጋ ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦የቡና ምርታቸውን በባለሙያ በመታገዝ በጥራት ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን የካፋ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን በበኩሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ74 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የመሰብሰብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
በካፋ ዞን የሺሾ እንዴ ወረዳ ሾራጠቃ ቀበሌ አርሶ አደር መልካሙ ቆጭቶ እንዳሉት፣ የቡና ምርታቸውን በጥራት በመሰብሰብ ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሠሩ ነው።
ምርት የሚሰጥ አንድ ሄክታር ቡና እንዳላቸው ጠቅሰው አምና 300 ኪሎ ግራም ቡና አቅርበው 400 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በባለሙያ ታግዘው ቡና በጥራት በመልቀም ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አንስተው፣ ከዚህም የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
1 ነጥብ 5 ሄክታር ቡና እንዳላቸው የገለጹት የቀበሌው አርሶ አደር ባሕሩ ወ/ሚካኤል፣ ከቡና ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን በጥሩ ሁኔታ እየመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አምና 2 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ቡና ሸጠው የተሻለ ገቢ ያገኙ ሲሆን፣ ዘንድሮም ምርቱን በጥንቃቄ በመሰብሰብ ለኢንዱስትሪዎች በጥራት እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከማሳ እንክብካቤ ጀምሮ እስከ ምርት ዝግጅትና አያያዝ ድረስ የባለሙያ ምክረ ሐሳብን ተከትለው መሥራት ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ጥቅም በማግኘት ላይ እንደሚገኙም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ምርትን በጥራት የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ74 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን ግብ ለማሳካት፣ የቡና ምርት አቅርቦት መጠንና ጥራት ማስጠበቅን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎችን የመደገፍና የመከታተል እንዲሁም በየደረጃው ያለውን የቡና ምርት ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ግብረ ኃይል የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ 318 የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ከአርሶ አደሩ የተቀበሉትን እሸት ቡና የማጠብ ሥራ ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት አጋማሽ 23 ሺህ 171 ቶን ቡና ማቅረብ መቻሉንም ተናግረዋል።