የባህር በር ጥያቄ እውን እንዲሆን የምናደርገውን አስተዋጽዖ አጠናክረን እንቀጥላለን - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ጥያቄ እውን እንዲሆን የምናደርገውን አስተዋጽዖ አጠናክረን እንቀጥላለን - ምሁራን
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ እውን እንዲሆን የምናደርገውን አስተዋጽዖ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ያነጋገራቸው ምሁራን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄው እውን መሆን ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአካባቢው ሀገራትም ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
በመሆኑም ጥያቄው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ከመንግስትና ከህዝብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በተጨማሪ የምሁራን አስተዋጽኦ በከፍተኛ ደረጃ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አበሻ ሺርኮ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዘመናት ከባህር በር ተነጥላ እንደማታውቅ ታሪክ ያሳያል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችበት መንገድ ሸፍጥ የታከለበትና ዛሬ ድረስ የታሪክ ስብራት ፈጥሮ ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ህጋዊና ትክክለኛ ጥያቄ በመሆኑ፣ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምሁሩ ተናግረዋል።
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ እውን መሆን የውጭ ንግድን ከማሳለጥ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ያሳድገዋል ብለዋል።
ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በሴራ የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት ውሳኔ ፍትሃዊነት የጎደለውና ህዝብም ያልመከረበት መሆኑን ያነሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህርና ተመራማሪ ተከተል ላቤና ናቸው።
የባህር በር ታሪካዊና ህጋዊ የባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ ያለው የዲፕሎማሲ ስራ የሚበረታታ መሆኑንም ምሁሩ ተናግረዋል።
በተለይም ታሪካዊ እውነታዎችንና ዓለም አቀፍ ህግን ባገናዘበ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርህና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ሊተገበር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የባህር በር ባለቤት ለመሆን የሚደረጉ ጥረቶች እውን እንዲሆኑ ምሁራን የተለያየ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጹት መምህርና ተመራማሪው፣ በጥናት የተደገፈ ምሁራዊ ትንታኔ ከመስጠት ጀምሮ ታሪክና የህግ አግባብን መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን አደራጅቶ ለመንግስት በማቅረብ መደገፍ አለብን ብለዋል።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የባህር በሯን ያጣችበትን ሴራ ለዓለም ማህበረሰብ የማሳወቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉም አክለዋል።