የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሁለት መርሐ ግብሮች ጅማሮውን ያገኛል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ሸገር ከተማ ከነገሌ አርሲ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከአራት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ የሰበሰበው ሸገር ከተማ በአምስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኑ በመጀመሪያ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ላይ ካስመዘገበው ድል በኋላ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በስምንት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።
ጨዋታው ሸገር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ነገሌ አርሲ በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ከመቻል በጊዜያዊነት ይረከባል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሀላባ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከቀኑ 10 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በአምስት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሀዲያ ሆሳዕና በአራት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
በአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሀላባ ከተማ በወላይታ ድቻ የ6 ለ 0 ሽንፈት ሲያስተናግድ ሀዲያ ሆሳዕና ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 በመርታት የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።
ሀላባ ከተማ ከሽንፈቱ አገግሞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
ሀዲያ ሆሳዕና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ጥቅምት 23 2019 ዓ.ም ይቆያል።
መቻል በዘጠኝ ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የወላይታ ድቻው መሳይ ሰለሞን በአራት ግቦች እየመራ ሲሆን የባህር ዳር ከተማው አንተነህ ተፈራ በሶስት ጎሎች ይከተላል።