ቀጥታ፡

የሩሲያና አፍሪካን ሁሉንአቀፍ ትብብር በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ተስማምተናል-ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን

ሞስኮ፣ጥቅምት 19(2019(ኢዜአ)፦የሩሲያና አፍሪካን ሁሉንአቀፍ  ትብብር በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ተስማምተናል ሲሉ ቭላዲሚር ፑቲን ገለጹ።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እና የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኤቨረስት ኑዳዪሺሚዬ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ማጠቃለያ መድረክን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው  ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እንዳሉት ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ለማጠናከር ዝግጁ ናት።

ሩሲያ እና የአፍሪካ ሀገራት ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ ትብብራቸውን ለማስፋት፣የሚገጥሙ እንቅፋቶችን በጋራ ለማስወገድ እና የገቢ ንግድን ለማሳደግ እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት።

ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤም ትብብሩን የበለጠ ለማጠናከር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልፀው ፣ሩሲያ የአህጉሪቱ የልማት ስኬቶች አካል መሆን ትሻለች ነው ያሉት።

አፍሪካ በትልቅ መነቃቃት ላይ የምትገኘ ብቻ ሳትሆን ተጨባጭ በሆነ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያለች በመሆኑ ሩሲያ በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ አግባብ በተለያዩ ዘርፎች የመሳተፍ ፍላጎት አላት።

ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤም ለባለብዙ ወገን ትብብር እና ለጋራ ብልጽግና ያለውን እያደገ የመጣ ቁርጠኝነት ማንፀባረቁን ጠቁመዋል።

አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚና ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወት እንደምትችል በመግለጽ፣ለዚህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላትን ውክልና ማሳደግ ተገቢ ነው ብለዋል።

ይህም ተሳትፎ  የራሷን የልማት አቅጣጫ በራሷ የመወሰን አቅሟን የሚያጠናክር ነው ያሉ ሲሆን የፀጥታው ምክር ቤት በስምምነት ላይ በተመሠረተ  ሁኔታ ሊሻሻል ይገባል።

በአፍሪካና በሩሲያ መካከል ያለው የንግድ እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ፣ትብብሩ በጥሬ ዕቃ ልውውጥ ብቻ ሳይገደብ በአካባቢያዊ ምርት እድገት፣በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እንዲያተኩር ይደረጋል።

በተጨማሪም በኃይል፣በመሠረተ ልማት፣በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ የሁለቱን ወገኖች ግንኙነት ይበልጥ እናጠናክራለን ብለዋል።

የምግብ ዋስትና ለአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ነፃነትና ዘላቂ የልማት እድገት ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ፑቲን ፣በዚህ ዘርፍ  የአህጉሪቱን የምርት አቅም ለማሳደግ ሩሲያ ቁርጠኛ ነች።

ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔም እያደገ የመጣውን አጋርነት በሚያንፀባርቅ መልኩ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም