በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ ውጤቶች መለወጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ ውጤቶች መለወጥ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን የታሪክና የወዳጅነት ትብብር ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ ውጤቶች መለወጥ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ወዳጅነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀ መሆኑን ገልጸዋል።
እ.አ.አ በ1888 ከአድዋ ጦርነት በኋላ የሩሲያ ቀይ መስቀል ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቆሰሉ አርበኞችን ማከሙንና የሕክምና መማሪያ መጽሐፍን ወደ አማርኛ መተርጎሙን አስታውሰዋል።
ይህ ታሪካዊ ክስተት እውቀትን ወደ ፈውስ የለወጠ አርአያነት ያለው ተግባር እንደነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የሚደረጉ ስምምነቶችም በተመሳሳይ ወደ ተጨባጭ ውጤት መተርጎም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዓለም እየተለወጠች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሀገራት በምርትና ሳይንስ በጋራ ማደግ ሙሉ ጥንካሬን እንደሚፈጥር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ መነሻ ሉዓላዊነትና የራስን የመወሰን አቅም ማሳደግ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥታ እየሰራችባቸው ባሉ ሶስት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምግብ ዘርፍ የሕዝብን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ዘላቂ የግብርና ኢኮኖሚ መገንባት የመጀመሪያው አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ትብብር በግብርና ማሽነሪዎች አቅርቦትና ምርትን በስፋት በሚያቀናብሩ ኢንዱስትሪዎች ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።
በኃይል ዘርፍ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በውሃ ኃይል ላይ የተመሰረተውን የኃይል አማራጭ ለማበልጸግ ከሩሲያ ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የዓለም አቀፍ የኒውክሌር ኤጀንሲን የደህንነት መስፈርቶች የተከተለ ሲሆን፣ የኒውክሌር ሳይንስ ከኃይል ማመንጨት ባለፈ የምግብ ብክነትን ለመቀነስና የካንሰር ሕክምናን ለማስፋት ይውላል ነው ያሉት።
ለዚህም የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን የማፍራትና የመቆጣጠር አቅም ለመገንባት ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በአሁኑ ዘመን በእውቀትና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የቴክኖሎጂ አቅም የሚለካው በሰው ሰራሽ አስተውሎት መሆኑን አበክረው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ ተመራማሪዎች በራሳቸው ቋንቋ መሣሪያዎችን መፍጠርና የመረጃ ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ በአዳማ ከተማ የአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ ዩኒቨርሲቲን እየገነባች መሆኑን ገልጸው፣ የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በማስተማርና በምርምር ዘርፍ አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የፈጠራ ሥራዎች ወደ ምርትና ንግድ መቀየር እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አፍሪካ በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በኩል አንድ ወጥ ገበያ እየገነባች በመሆኗ፣ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ውስጥ በመድኃኒትና በማሽነሪ ዘርፍ የጋራ ኩባንያዎችን በመሥረት ለአህጉሪቷ ምርት እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የንግድ ልውውጡን ቀላልና ተመጣጣኝ ለማድረግ በሀገራቱ መካከል ያሉ የክፍያ ስርዓቶችን ማቀናጀት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ግጭቶችን በድርድር ለመፍታት፣ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካውያን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ለሁሉም ሀገራት ያለ ምንም ልዩነት በእኩልነት እንዲከበርና እንዲተገበር በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።
የኢትዮጵያን የመደመር ፍልስፍና ከሁለቱ ሀገራት ታሪክ ጋር በማያያዝ፣ ከ130 ዓመታት በፊት የሩሲያ ሕክምና መጽሐፍ ወደ አማርኛ እንደተተረጎመ ሁሉ፣ ዘንድሮ ደግሞ የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ መተርጎሙን ጠቅሰዋል።
ይህም የእውቀት ልውውጥ ሁሉን አቀፍ እውነተኛ አጋርነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ጊዜ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ወደ አፍሪካ ሲመጣ የአፍሪካ ህብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አስተናጋጅ ለመሆን ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።