ቀጥታ፡

ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ (ዲተረንስ)

ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ (ዲተረንስ)

ጦርነትን በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ሳይጀመር በማስቀረት የሚገኝ ድል ከሁሉ የላቀ ነው። ጥንታዊው የቻይና ጦር ስትራቴጂስት ሱን ዙ "ዘ አርት ኦፍ ዋር" በተሰኘው መጽሐፉ፣ ትልቁ የጦር ጥበብ ጠላትን ሳይዋጉ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሆነ ጽፏል። በዚህም መፅሐፉ መቶ ጦርነትን አሸንፎ መገኘት የላቀ ጥበብ አይደለም፤ ምክንያቱም ድል መንሳት በራሱ የሰው ሕይወትና የአገር ሀብትን ያስከፍላልና። ይህ ሃሳብ በዘመናዊው የደህንነት ጥናት ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ ወይም "ዲተረንስ" ተብሎ ይጠራል። የትርጉሙ ጭብጥም ጠላት ጥቃት ከመሞከር እንዲታቀብ የሚያደርግ እምነትን መፍጠር ነው።

ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ መሠረታዊ አመክንዮ ማንኛውም ወገን ጦርነት የሚጀምረው ከጦርነቱ የሚያገኘው ጥቅም ከሚከፍለው ዋጋ እንደሚበልጥ ሲያስብ ነው። ስለዚህ አንድ አገር የጥቃትን ዋጋ በበቂ ሁኔታ ካናረ፣ ጠላት ሒሳቡን ሲሰራ ጦርነት ኪሳራ ሆኖ ይታየዋል። ሮማዊው ወታደራዊ ጸሐፊ ቬጌቲየስ ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በፊት በጻፈው መፅሓፍ የከተበው ታዋቂ አባባል ይህንኑ ይገልጻል። "ሰላምን የሚሻት ቢኖር ለጦርነት ይዘጋጅ" ይላል።

ይህም በተለያዩ አስረጂ ጉዳዮች ሊዳሰስ ይችላል፤ የመጀመሪያው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ነው። የአየር መከላከያ፣ የመድፍና የሚሳይል አቅም፣ የታጠቁ ኃይሎችና የአየር ኃይል ብቃትን ይመለከታል። ሁለተኛው የሰለጠነ ወታደር ነው፤ ምክንያቱም መሳሪያ በብቁ እጅ ካልተያዘ ክብደት እንጂ ጉልበት አይሆንምና። ተከታታይ ስልጠና፣ ዲሲፕሊንና የዕዝ ሰንሰለት ያለው ሠራዊት ለጠላት ከሚታየው ቁጥር በላይ ግምትን ይፈጥራል። ሦስተኛው በቴክኖሎጂ የታገዘ የውጊያ ብቃት ነው፤ ይኸውም ስለላና የስለላ ድሮኖች፣ ሳይበር፣ የመገናኛና የመረጃ ሥርዓት እንዲሁም ትክክለኛ ኢላማን የመምታት አቅምን ያካትታል። በዘመናችን ጦርነት የሚወሰነው በመረጃ የበላይነት ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ጠላቱን አስቀድሞ የሚያይ ወገን ሁልጊዜም አንድ እርምጃን ቀድሟል።

ሌላኛው ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚዘነጋው ተዓማኒነት ነው። አሜሪካዊው የስትራቴጂ ምሁር ቶማስ ሼሊንግ “Arms and Influence” በተሰኘው መጽሐፉ እንደሚያስረዳው፣ ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ ወይም "ዲተረንስ" የሚሰራው አቅሙ ብቻ ሳይሆን ያንን አቅም የመጠቀም ፍላጎትና ቁርጠኝነት ጭምር ለጠላት ግልጽ ሲሆን ነው። ምስጢር ሆኖ የተቀመጠ ወይም በማሳየት ያልተረጋገጠ አቅም ጠላትን ሁለቴ ደጋግሞ እንዲያስብ ሊያደርገው አይችልም።

ለዚህም ነው ወታደራዊ ልምምዶች፣ ሰልፎችና ግልጽ የመከላከያ ፖሊሲዎች የጥበቡ አካል የሆኑት። የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ልምድም ይህን ያሳያል፤ ሁለቱ ልዕለ ኃያላን አሜሪካና የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት የጋራ ጥፋት የሚያስከትል የኒውክሌር አቅም ስለነበራቸው በቀጥታ ከመዋጋት ተቆጥበው በቃላት ጦርነት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።

ኢትዮጵያም ለዚህ ጉልህ ታሪካዊ ምሳሌ አላት። በ1888 ዓ.ም. በዓድዋ አፄ ምኒልክ  ከየአቅጣጫው የተሰበሰበውን ሕዝብ በአንድ ዓላማ አሰልፈው፣ እቴጌ ጣይቱንና ሌሎች የጦር መሪዎችን አስተባብረው ጣሊያንን በሚወስን ሁኔታ ድል አድርገዋል። ድሉ ከውጊያ ሜዳ ባሻገር ዲፕሎማሲያዊ ውጤትም ነበረው፤ በዚያው ዓመት በተፈረመው የአዲስ አበባ ውል ጣሊያን የኢትዮጵያን ነጻነት እንድታውቅ ተገደደች። ለሌሎች የአውሮፓ ኃያላንም ኢትዮጵያን መውረር ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ጠንካራ መልዕክት በመሆን ሌላ ጦርነትን ለማስቀረት አገለገለ። ይህ ጦርነትን የማስቀረት ጥበብ በተግባር የተፈተነ አቅሙ ታይቷል፣ ቁርጠኝነቱም ተረጋግጧል።

አሁን ላይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ ባላት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ምክንያት ለውስጣዊና ለውጫዊ ጫናዎች ተጋላጭ ሀገር ናት። ሀገሪቷ የምትገኝበት መልክዓ ምድር በተለያዩ ግጭቶች የሚታወቅ ብቻም ሳይሆን የተለያዩ ኃያላን አገራት ጦር የሚገኝበት ቀጣና ነው። ይህንን ከግምት ባስገባ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሠራዊቱን በማዘመን ረገድ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዷል እየወሰደም ይገኛል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት አከባበር በዓል ላይ አየር ኃይሉን በማዘመን በ2030 ከአራተኛ ትውልድ ወደ አምስተኛ ለማሻገር እንደሚሰራ መናገራቸው ይታወሳል። አየር ኃይሉ አሁን ካለበት በዕጥፍ የማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አስረግጠው ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በራሱ ጠላት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃትን ከመፈፀሙ በፊት ሁለቴና ሦስቴ እንዲያስብበት የሚያደርግ መሆኑን ማንሳቱ ግድ ይላል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከቃል በላይ ለመሆኑ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ አየር ኃይሉ ከዚህ ቀደም ከታጠቃቸው ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ትናንት 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶችን ከሩሲያ ተረክባለች። በዚህም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት በሰላሙ ጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅት ባለማድረጋቸው ምክንያት ችግር ሲፈጠር ለአደጋ ሲጋለጡ እንደሚታይ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ላለማስደፈር በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የተረከበቻቸው የሱ-35 ኤርክራፍቶች በዓለም ላይ ካሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ግንባር ቀደም ናቸው። መሳሪያዎቹ ከአየር ወደ አየር እንዲሁም ከአየር ወደ ምድር ውጊያ የማካሄድ ከፍተኛ አቅም ያላቸውና በተግባር የተፈተኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጡ የክሩዝ ሚሳኤል ጥቃቶችን እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት የመለየት (Detect) እና የማክሸፍ (Intercept) ብቃት እንዳላቸው አስረድተዋል። ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ለሀገር ህልውና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል የነበሩት የሱ-30 እና የአሁኖቹ የሱ-35 ተዋጊ ጄቶች የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄት ባለቤት ከሆኑ በጣት የሚቆጠሩ አገራት መካከል አትዮጵያ አንዷ መሆኗ ደግሞ ከራሷ ሉአላዊትንም ባለፈ ለአህጉሩ እና ለቀጣናው ሰላም መጠበቅ ወሳኝ ሚና ይኖራታል ማለት ነው። ምክንያቱም የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄት በዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ የአየር ላይ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችል ዘመናዊ ተዋጊ ጀት ነው። የጀቱ ሞተሮች አቅጣጫቸውን መቀየር የሚችሉ (3D Thrust Vectoring Nozzles) በመሆናቸው አየር ላይ ባልተለመዱ ማዕዘኖች እና ፍጥነቶች እንዲንቀሳቀስ ያስችሉታል።

የሩሲያ አየር ኃይል ከሚጠቀማቸው እጅግ ዘመናዊ እና አደገኛ የጦር ጄቶች መካከል አንዱ ነው። የዚህ ጀት መገለጫ እጅግ ዘመናዊና ተዋጊ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የ5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ የተቀላቀለበት ስለመሆኑም ይነገራል። በሰአት 2 ሺህ 400 ኪ.ሜ የመብረርና ያለተጨማሪ የነዳጅ ታንከርም 3 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር መብረር የሚችለው ተዋጊ ጀት በአንድ ጊዜ እስከ 30 ኢላማዎችን የመከታተል እና 8ቱን በአንድ ጊዜ የመምታት አቅም አለው።

ራዳሩን ሳያበራ (ምንም ዓይነት የራዳር ሞገድ ሳይለቅ) በኢንፍራሬድ/ካሜራ (IRST) አማካኝነት ጠላትን በድብቅ እስከ 80 ኪ.ሜ ርቀት ድረስ መከታተል ይችላል። የጠላት ራዳሮችን እና ሚሳይሎችን በመረበሽ (Jamming) ጄቱን ካልተጠበቀ ጥቃት ይከላከላል። የሩሲያ አየር ኃይል ከሚጠቀማቸው እጅግ ዘመናዊ እና አደገኛ የጦር ጄቶች መካከል አንዱ ነው። የዚህ ጀት መገለጫ እጅግ ዘመናዊና ተዋጊ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የ5ኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ የተቀላቀለበት ስለመሆኑም ይነገራል።

ለዚህም ነው በሩሲያ በተደረገው የጦር ጀቶቹ ርክክብ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ያሉት። ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም የገነባች መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የየብስ፣ የአየርና የባህር ኃይሎች በሳተላይትና በዲጂታል የመገናኛ መረቦች እንዲተሳሰሩና እንደገና እንዲደራጁ መደረጉም ጠላት ሁለቴ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው። ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ብቁና ጠንካራ ሠራዊት የስለላ፣ የትክክለኛ ጥቃትና የፈጣን ምላሽ አቅምን ስለሚጨምር የአየር ክልልን የመጠበቅ ችሎታን ያሳድጋል። ይህ ሁሉ አንድ ላይ ሲታይ ኢትዮጵያን በቀላሉ ለማጥቃት እንደማይቻል የሚያስተላልፈው መልዕክት የጎላ ነው። እውነተኛ ድል ጥይት ሳይተኮስ በሚገኝ ሰላም ይረጋገጣል!!! የሚባለውስ ለዚህ አይደል!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም