የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ችሎት በተሞክሮነት የሚወሰድ ተምሳሌታዊ አሰራር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ችሎት በተሞክሮነት የሚወሰድ ተምሳሌታዊ አሰራር ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ችሎት በተሞክሮነት የሚወሰድ ተምሳሌታዊ አሰራር መሆኑን የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ልዑካን ቡድን አባላት ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
ከትናንት ጥቅምት 18 ጀምሮ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤቶች የልምድ ልውውጥ መድረክ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ልዑካን ቡድን አባላትም የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት፣ የኢትዮጵያ ስቶክ ገበያ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጎብኝተዋል።
የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት ሊቀመንበር ኔሚ ኪለካጄንጋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት በቴክኖሎጂ የታገዘ አስደናቂ ሥራ እየሠራ ነው።
በተቋማቱ ጉብኝት ያገኙትን ልምድና ተሞክሮም በታንዛኒያ በመተግበር ዘመናዊና ስሉጥ አሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልህቀት የፋይናንስ ዘርፍ የአቤቱታ ጉዳዮችን አፋጣኝና ግልጽ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት፣ የኢትዮጵያ ስቶክ ገበያ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አሠራርም ልምድና ተሞክሮ የቀሰሙበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዲጂታል ሽግግርም አፍሪካውያንን ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለማሳለጥ በአርዓያነት የሚወሰድ አሠራር መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም የአፍሪካን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር በማሳለጥ መልኩ በታንዛኒያ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል።
የታንዛኒያ የካፒታል ገበያ ፍርድ ቤት የሕግ ባለሙያ ኤልያድ ኢ-መንደም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የቴክኖሎጂ ችሎት ተምሳሌታዊ ነው ብለዋል።
ይህም ለፋይናንስ አለመግባባት ችሎቶች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥና ታንዛኒያም በተሞክሮነት የምትቀስመው አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።