ቀጥታ፡

አመራሩ ከሕብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ  በቁርጠኝነት ይሰራል -ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) 

ሆሳእና፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራሩ  ከልማት ተጠቃሚነትና ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር በተያያዘ ከሕብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተካሄደውን ህዝባዊ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ በክልሉ የማህበረሰቡን የሰላም ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቷል።

በዚህም በክልሉ በሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች  ከህዝቡ ጋር ውይይት መደረጉን በማስታወስ የተካሄዱ ውይይቶች የህዝቡን ጥያቄዎች በተደመረ አቅም ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚያስችል መደላድል የተፈጠረበት መሆኑን አመልክተዋል።

በምክክር መድረኮቹ  የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የልማትና በመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መነሳታቸውን ጠቅሰዋል።

በመድረኮቹ የመንገድ ፣ የመብራት ፣ የኔትወርክ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የሌሎች ማህበራዊ ተቋማትና የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና የፕሮጀክቶች መጓተት ችግሮች መነሳታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለያየ ምክንያት ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንዲደረጉ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።

አመራሩ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በማመላከት በውይይት መድረኮቹ  ህዝቡ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ልምዱን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግሥት የማህበረሰቡን አቅም አስተባብሮ በመጠቀም ለክልሉ ፈጣን ልማት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም