የመንግሥት የቦንድ ሽያጭ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር የሚያስችል ውጤታማ አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት የቦንድ ሽያጭ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር የሚያስችል ውጤታማ አቅም የሚፈጥር ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ መንግሥት የቦንድ ሽያጭ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን በመቆጣጠር የበጀት ጉድለትን መሸፈን የሚያስችል ውጤታማ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንዳሉት፤ የቦንድ ሽያጭ መንግሥታት የዋጋ ግሽበትና ተያያዥ የኑሮ ጫናን ለመከላከል ከባንክ ብድር ከመውሰድ ይልቅ የቦንድ ሽያጭ በማካሄድ ክፍተቶችን ለማቃለል የሚጠቀሙበት አማራጭ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።
የቦንድ ሽያጩም ግለሰቦች ገንዘባቸውን ወደ መንግሥት በማስተላለፍ መንግሥትም የተላለፈውን ገንዘብ ልማትን በማሳለጥ የበጀት ጉድለቶችን መሙላት የሚችልበት ሥርዓት መሆኑን አንስተዋል።
የቦንድ ሽያጭ የአሰራር ሥርዓቱም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ መረጨትን በመግታት የዋጋ ግሽበትንና የዜጎችን የኑሮ ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።
የአሰራር ሥርዓቱም የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተሞክሮ መሆኑን አስረድተዋል።
የበርካታ ሀገራት መንግሥታትም የበጀት ጉድለታቸውን በቦንድ ሽያጭ በመሸፈን የዜጎቻቸውን ልማትና መሻት እንደሚያሳልጡ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ያለተጨማሪ ብድር የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የከፈተው የቦንድ ሽያጭ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱ በማድረግ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሙሴ በየነ በበኩላቸው፤ የመንግሥት የቦንድ ሽያጭ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የበለጸጉ ሀገራት ጭምር የበጀት ጉድለታቸውን በቦንድ ሽያጭ የሚሸፍኑበት ውጤታማ ዓለም አቀፍ አሰራር መሆኑንም አስታውቀዋል።
ለቦንድ ሽያጭ ውጤታማነትም የካፒታል ገበያ ወሳኝ ነው ያሉት ምሁሩ፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያም የመንግሥትን የቦንድ ሽያጭ ውጤታማነት ለማላቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የቦንድ ሽያጭም የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በቂ ገንዘብ በእጁ በማስገባት በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ለማድረግ የሚያስችለው መሆኑን አስረድተዋል።