ቀጥታ፡

የባሕር ዳር ከተማ የክትመት ሥልጣኔ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ ዕድገት እያመጣች መሆኑን ያሳያል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ የባሕር ዳር ከተማ የተሰናሰለ የሐይቅ ዳርቻ ክትመትና የመሰረተ ልማት ሥርዓት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ ዕድገት እያመጣች መሆኑን እንደሚያሳይ የ12ኛው የጣና ፎረም ተሳታፊዎች ገለጹ። 

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

12ኛው የጣና ፎረም "በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ ፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በውቢቷ ባሕር ዳር ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል። 

የአፍሪካ ሀገራት የአሁንና የቀድሞ መሪዎች፣ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጭዎች በጣና ፎረም ላይ ታድመዋል፤ የባሕር ዳርን የክትመት ሽግግርም አድንቀዋል። 


 

በናይጀሪያ የኦባፌሚ አዎሎዎ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ቻርለስ ዑኬጄ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባሕር ዳር በተደጋጋሚ ብትጎበኝም ከተማዋ ሁል ጊዜም መንፈስን የምታድስ ከተማ ናት። 

የባሕር ዳር ከተማ በአውሮፕላን ጣቢያ፣ በትልልቅ የኪነ-ሕንጻና ማራኪ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ከፍተኛ ጥራት ባለው የክትመት መሰረተ ልማት ሽግግር ላይ መሆኗን ገልጸዋል። 

የጣና ዳር ፈርጧ ባሕር ዳር አስደናቂ የመሰረተ ልማት ግንባታና የክትመት ሽግግርም የሰው ልጆችን የዕድገት መሻት የሚገልጡ ተግባራት መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በውቢቷ ባሕር ዳር በየዓመቱ በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዙሪያ የሚመክር የጣና ፎረም የአህጉሪቱ ትልቁ መድረክ በመሆኑ የከተማዋን ዓለም አቀፍ ገጽታ ለማጉላት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል። 

የአፍሪካ የአየር ንብረት ፎረም ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጆርጅ ንዋንግው በበኩላቸው፤ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ባሕር ዳር ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፤ ከተማዋም ማራኪና አስደናቂ ገጽታ የተላበሰች ናት ብለዋል። 


 

የባሕር ዳር ከተማን ውበትና አስደናቂነት ከዚህ ቀደም እንደማያውቁ በመጠቆም፤ የከተማዋ ሕዝብ ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕልም ልብን የሚገዛ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞቿ ያመጣችው አስደናቂ ለውጥ ባሕር ዳርን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ መፍጠሩን አንስተዋል። 

የባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ጸጋዎች በሚገባ በማስተዋወቅ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማላቅ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። 

ባሕር ዳር የሐይቅ ዳርቻ የክትመት ሥልጣኔን አጣጥማ የያዘች ናት ያሉት ደግሞ በአፍሪካ የደኅንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ፖል ሲሞን ሃንዲ (ዶ/ር) ናቸው። 


 

የባሕር ዳር ከተማ ከተጎናጸፈችው አስደናቂ የሐይቅ ዳር ውበትና የመሰረተ ልማት ባሻገርም ጣፋጭ ዓሳ የሚመረትባት ዐይነ ግቡ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። 

የባሕር ዳር ከተማ ፈጣን ዕድገትና የክትመት ሥልጣኔም ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ ዕድገት ያመጣች መሆኗን እንደሚያሳይ አመላክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም