ቀጥታ፡

ፈቃዱ ተሰርዞ የነበረው “ድምጺ ወያነ” “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” በሚል ስያሜ የብሮድካስት ፈቃድ ተሰጠው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ ቀደም ሲል የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃዱ የተሰረዘው “ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት”በአዲስ ስያሜ “ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት” የሚል የብሮድካስት ፈቃድ ተሰጥቶታል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።

ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎትን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር፣ ጣቢያው ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረኑ ይዘቶችን በሕገወጥ መንገድ ሲያሰራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ መሰረዙ ይታወሳል።

የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደርም ፤ ቀደም ሲል ድምጺ ወያነ ትግራይ ሬድዮና ቴሌቪዥን በሚል የሬድዮና ቴሌቪዥን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ጣቢያ የጦርነት መሳሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ እንደተሰረዘ አስታውሷል።

አሁን ክልሉን የሚመራው የባለአደራ አስተዳዳር የክልሉን ሰላምና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የስያሜ ለውጥ በማድረግ ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል በአዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ባለአደራ አስተዳደሩ ያቀረበውን ጥያቄም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣንም ከመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አንፃር በመመርመር ጥያቄው ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን መቀበሉን አስታውቋል።

ስለሆነም ባለሥልጣኑ ማእዶት ብሮድካስቲንግ አገልግሎት በሚል አዲስ ስያሜ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን በማሳወቅ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስት አገልግሎቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም