ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፦በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት መልዕክቴን ማስተላለፍ በመቻሌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
በዚህ ታሪካዊ መድረክ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህም በምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፣ በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም በክህሎት እና በዕውቀት ሽግግር ላይ የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት መሆኑንም አንስተዋል።
ይህንን ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከሩሲያ ጋር በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል።
ይህ ስትራቴጂካዊ ትብብር የኃይል አማራጮቻችንን ከማስፋት ባለፈ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት ትስስር ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።