በሰሜን ጎንደር ዞን በበጋ ወራት 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ተግባር ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎንደር ዞን በበጋ ወራት 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ተግባር ተገብቷል
ጎንደር፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ በሰሜን ጎንደር ዞን በተያዘው የበጋ ወራት 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ተግባራዊ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ የመስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ተክለማርያም ገብረሥላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ ካለፉት ዓመታት ከታየው ተሞክሮ በመነሳት የበጋ መስኖ ልማት በስፋት ይከናወናል።
በዚህም በተያዘው የበጋ ወቅት በመስኖ ልማት በአጠቃላይ 11 ሺህ 256 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
አጠቃላይ በዘር ከሚሸፈነው መሬት 3 ሺህ ሔክታር የሚሆነውን በበጋ ስንዴ ልማት በመሸፈን ከ96 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።
የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በዞኑ ጃናሞራ ወረዳ የወይና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታዘበው ፈቃዱ እንዳሉት በመስኖ ልማት ስንዴ ማልማት በመቻላቸው በፊት ሲያገኙት ከነበረው በተሻለ ምርታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ባለፈው ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ስንዴ በኩታ ገጠም በማልማት 14 ኩንታል ምርት በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የስንዴ ልማት ከምርቱ በተጨማሪ ተረፈ ምርቱን ለእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥራ በማዋል ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያስቻላቸው በመሆኑ ዘንድሮም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የበየዳ ወረዳ ጃንበሎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሀባው አስረስ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በመስኖ ስንዴ ልማት ተሳትፈው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ተደራጅተው በክላስተር ማልማታቸው ሰብልን በጋራ በመንከባከብ ምርታማነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ የተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
በሰሜን ጎንደር ዞን በተያዘው የበጋ ወቅት በመስኖ ከሚለማው መሬት ከ360 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ተመላክቷል።