በሸገር ከተማ አስተዳደር የግብርናውን ዘርፍ የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ አስተዳደር የግብርናውን ዘርፍ የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሸገር ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ) ፦ ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት፣ ጥራት ያለው ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት እና የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሸገር ከተማ አስተዳደር በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና አርሶ አደሮች በተገኙበት የተለያዩ የግብርና ልማትና የቤተሰብ ብልጽግና ኢንሼቲቮች የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
በመስክ ምልከታው የዶሮ እርባታ፣ የገብስና ስንዴ የኩታ ገጠም ልማት፣ የወተት ላም እርባታ፣ የሙዝ ክላስተር እና የተመራጭ የገብስ ዘር ማባዛት ኢንሼቲቮች ተጎብኝተዋል።
ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ ጠንካራ ኢኮኖሚ የመገንባት፣ ጥራት ያለው ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት እና የግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚን የማዘመን ግቦቹን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ሸገር ከተማ በጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሠረት ላይ የተገነባ ዘመናዊ ከተማ የመሆን ራዕዩን እውን እያደረገ ይገኛል ያሉት ከንቲባው፤ ከተማው ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ግልጽና ስልታዊ የሆኑ ዕቅዶችን በመቀየስ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
በከተማው በተከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውጤቶች መገኘታቸውን የገለጹት ዶክተር ተሾመ፤ በተለይም የግብርና ኢንሼቲቮችንና የቤተሰብ ብልጽግናን ውጤታማ ለማድረግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማምረት እና የግብርና ግብአቶችን በወቅቱ ማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
እውነተኛ ነፃነትና ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው በልማት ሥራዎች ላይ በሚደረግ ቁርጠኛ ትኩረት ብቻ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ተሾመ አሁንም የጀመርናቸውን የልማት ሥራዎች አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።
ሸገርን ልዩ የሚያደርገው ለግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሰጠው ትኩረት ሲሆን፤ የሚከናወነው የግብርና ስራም ለሰው ልጅ ህልውና መሠረት፣ ለፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ዋነኛ የግብአት ምንጭ እንዲሆን ተደርጎ መሆኑን አንስተዋል።
በከተማው ለአርሶ አደሮች በተሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እና በወቅቱ በቀረቡ የግብርና ግብአቶች ምክንያት፣ ቀደም ሲል በሄክታር ከ35 ኩንታል በታች የነበረውን የምርት መጠን በአሁኑ ወቅት ወደ 47 ኩንታል ለማሳደግ እየተቻለ ነው ብለዋል።
የመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አህመዲን እስማኤል በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት የህብረተሰቡንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በተከናወኑ የግብርናና የቤተሰብ ብልጽግና ኢንሼቲቮች በክፍለ ከተማው ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።