ቀጥታ፡

ብሪክስ ከአፍሪካ ጋር ያለውን የኢንዱስትሪ ትብብር ለማጠናከር አዳዲስ አሰራሮችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19 /2019 (ኢዜአ)፦ ብሪክስ ከአፍሪካ ጋር ያለውን የኢንዱስትሪ ትብብር ለማጠናከር አዳዲስ አሰራሮችን ይፋ አድርጓል።

ይህ የተገለጸው በሞስኮ በተካሄደው በሶስተኛው የሩሲያ–አፍሪካ ጉባኤ “የብሪክስ መድረክ ለሩሲያ-አፍሪካ የንግድ ትብብር እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው  የውይይት መድረክ ላይ ነው።

የሩሲያ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ማክሲም ረሼትኒኮቭ፣ ብሪክስ ለአፍሪካ ሀገራት ክፍት የሆነ ገበያ ከመሆኑም በላይ የቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች እና የኢንቨስትመንት አቅርቦት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ እየተዘጋጁ ካሉ አዳዲስ አሰራሮች መካከል የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማህበር እና የእህል የንግድ ልውውጥ (Grain Exchange) ይገኙበታል።

በተጨማሪም የአባል ሀገራቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች የኢንዱስትሪ ዲጂታላይዜሽን እና የቴክኖሎጂ ትብብር ማዕቀፍ እንዲዘረጋ ሀሳብ ማቅረባቸውን የቲቪ ብሪክስ ዘገባ ያመለክታል። 

ረሼትኒኮቭ አክለውም፣ ብሪክስ አሁን ላይ ትብብሩን ከፖለቲካዊ ውይይት ባለፈ ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ እንደሚገኝና የመንግስታት እንቅፋቶችን በማስወገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ለአሰራሮች ውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እና ሩሲያ መካከል የኢንዱስትሪ ትብብር ዞን መፈጠሩ ለሁለቱ ወገኖች ትስስር መጠናከር የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት በስብሰባው ላይ ተመላክቷል።

በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ በመሰረተ ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስ፣ በኃይል እና በሳይበር ደህንነት ዘርፎች ውጤት የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን በጋራ መተግበር እንደሚገባ ተመላክቷል።

የብሪክስ (BRICS) አባል ሀገራት ነጻ የሆነ የክፍያ ስርዓት የመዘርጋት፣ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ አሰራሮችን የመፍጠር እና የኢንዱስትሪ ትብብራቸውን የማስፋት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝም እንዲሁ።

የስብሰባው መሪና የሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ የአፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኢሪና አብራሞቫ በአሁኑ ወቅት ከ37 ሺህ በላይ የአፍሪካ ተማሪዎች በሩሲያ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሆኑ መግለጻቸውን የቲቪ ብሪክስ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም