ቀጥታ፡

ከውበት ባሻገር

ከተሞች የሕዝብ መኖሪያ ብቻ ሳይሆኑ የኢኮኖሚ እድገት፣ የማኅበራዊ ትስስር፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ማዕከላት ናቸው። የከተሞች ልማትና ዘመናዊ አሰራር የአንድን አገር ህዝብ የኑሮ ደረጃ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የወደፊት የልማት አቅጣጫ የሚወስን ነው። በመሆኑም የከተሞች ልማት ከውበት ባሻገር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የማሻሻልና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ጉዳይ ሆኖ ይወሰዳል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የከተማ ልማት መሰረታዊ ለውጥ፣ እድገትና ማንሰራራት የታየበት መሆኑን መናገር ይቻላል። ከአፍሪካ መዲና እና የዓለም የዲፕሎማቶች ማእከል ከሆነችው አዲስ አበባ የጀመረው የኮሪደር ልማት ሌሎች ከተሞችንም አዳርሷል። የከተሞች የኮሪደር ልማት ከጅግጅጋ እስከ ወለጋ፣ ከሀረር እስከ ባህር ዳርና ጎንደር፣ ከሰመራ እስከ ጋምቤላ፣ ከሀዋሳ እስከ አሶሳ፣ ከጅማ እስከ አዳማና ነቀምት፣ በአርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳእና እና ሌሎችም ከተሞች ተስፋፍቷል። 

የከተሞቹ ልማት በተቀናጀ የከተማ ፕላን የሚመራ የወንዝ ዳር ልማትን ጨምሮ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎችና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማካተት እየተከናወነ ይገኛል። 

ከትራንስፖርት፣ ከውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከመብራት፣ ከቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ጋር ተሰናስሎ እየተገነባ ነው። በመሆኑም የስማርት ከተሞች ግንባታ ለነዋሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ መሳለጥ ብሎም ወንጀልን ለመከላከል አስችሏል። የከተማ ወንዞችን በማልማት፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋፋትና ለእግረኞችና ለሳይክል ተጠቃሚዎች ምቹ መንገዶችን በመገንባት የተሻለ ህይወት እንዲመሩና እንዲኖሩ እየተደረገ ነው። በልማቱ የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያን፣ የሕፃናትና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን ማእከል ያደረገ ሰው ተኮር ብሮጀክት መሆኑም ይታወቃል።

የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማትን በማሰናሰል በምርት አቅርቦት፣ በገበያ ትስስር፣ በትራንስፖርትና ሌሎችም አገልግሎቶች የተገናኙ እንዲሆኑ እየተደረገም ይገኛል። የከተሞችና የገጠር ልማት ትስስሩም የኢኮኖሚ እድገትን፣ እኩልነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን፣ የአካባቢ ጥበቃንና ሌሎችንም መሰረት ያደረገ መሆኑም ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የከተማ ልማት ከውበትና ምቾትም የተሻገረ ሀገር የመገንባት ስትራቴጂ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።

የ2026 ዓለም አቀፍ የከተሞች ቀን “Regenerating the City: Adequate Housing for All” “ከተሞችን ማደስ፤ የተሟላ መኖሪያ ቤት ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም በመላው ዓለም ይከበራል። የክብረ በዓሉ መልእክትም የከተሞችን የወደፊት አቅጣጫ ከሰው ልጆች ደህንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከኢኮኖሚያዊ እድገትና ከሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጋር በማስተሳሰር ነው።  ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የከተማ ልማት ከማደስና ዘመናዊ አድርጎ ከመስራት ባሻገር የዜጎችን ህይወት የመለወጥ ዓላማን የሰነቀ መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም