ቀጥታ፡

ሀገራዊ የወል ትርክቶችን ግንባታ ማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ዋነኛው መፍትሔ ነው - ምሁራን

ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)-የዜጎችን አብሮነት የሚያጎለብቱ ሀገራዊ የወል ትርክቶችን ግንባታ ማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ በሀገሪቱ የተጀመሩ የጋራ ትርክት ግንባታ ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ ትርክት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ አዎንታዊ ሚና  ስላለው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በአግባቡ መጠቀም ይገባል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ እንዳሉት አሰባሳቢ ትርክት ለአንድ ሀገር ሰላም፣ መልካም ገጽታና ሕልውና መሠረት ከሚጥሉ ጉዳዮች አንዱ ነው። 

በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ትርክት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሁሉ፣ ለቀጣይ ትውልዱ በእውነት ላይ የተመሰረተ የሀገር ታሪክ  ለማውረስ አሰባሳቢ የጋራ ትርክት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የዜጎችን አብሮነት የሚያጎለብቱ አገራዊ የወል ትርክቶችን መገንባት ለዘላቂ ሰላምና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን አስታውቀዋል።

አሰባሳቢ የወል ትርክቶችን ለመገንባት በመደመር መንግሥት እየተደረገ ያለው ጥረት እንደሚበረታታ መምህር አጥናፉ ገልጸው፣ ትውልዱም  ዘመኑን ለሚመጥን ብሔራዊ ትርክት ይበልጥ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።

በአገሪቱ የተጀመሩ የጋራ ትርክት ግንባታ ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የተዛቡ ትርክቶችን ለማረም እንደ ሀገራዊ ምክክር ያሉ የመፍትሔ አማራጮች ካላቸው ጥቅም በተጨማሪ ምሁራን የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል። 

የዜጎችን አንድነት የሚያጠናክሩ አሰባሳቢ ትርክቶችን በትውልዱ ላይ ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የምሁራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ በኩል የድርሻዬን እወጣለሁ ሲሉ አረጋግጠዋል።


 

"በሀገራችን የእርስ በእርስ ግጭትና የፖለቲካ ልዩነት የሚፈጥሩ ትርክቶች በጠላቶች ተተክለው ያለፉ ናቸው" የሚል አቋም እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በርሁን ናቸው።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ወደእኛ ሐሰተኛ ትርክቶችን በማምጣት መትከላቸውን አስታውሰው፣ "አሁን ያንን ሀሰተኛ ትርክት መስበር የሚቻልበት ጊዜ ላይ ነን" ብለዋል።

 ለዚህ ደግሞ "ሀገር ምን ትፈልጋለች?" በሚል አስተሳሰብ ከግል ጥቅምና ፍላጎት የራቀ ሀገራዊ እይታን ማስፋት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ የወል ትርክቶችን መገንባት የዜጎችን ሰላምና አብሮነት በዘላቂነት ለማጽናት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሰባሳቢ ትርክት ለሀገራዊ መረጋጋት፣ ሰላምና ልማት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት ማየትና መቅረጽ ከመንግሥት፣ ከሕዝብና ከምሁራን እንደሚጠበቅ መምህሩ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም