የመኸር በረከት፤ የምግብ ሉዓላዊነት መሰረት - ኢዜአ አማርኛ
የመኸር በረከት፤ የምግብ ሉዓላዊነት መሰረት
ኢትዮጵያ በአራቱ ወቅቶች የተሸለመች፣ በእርሻና በተፈጥሮ በረከት የተባረከች ምድር ናት። ከእነዚህ ወቅቶች መካከል ደግሞ "መኸር" ለአርሶ አደሩና ለአጠቃላይ ሕዝቡ ልዩ ትርጉም ያለው፣ የድካም ውጤት የሚታይበትና የተስፋ ፍሬ የሚለቀምበት ወርቃማ ወቅት ነው። የመኸር በረከት፤ የምግብ ሉዓላዊነት መሰረት ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። የአረንጓዴው የመስክ ገጽታ ወደ ቢጫና ወርቃማ ቀለም በሚቀየርበት በዚህ ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የደስታ፣ የሥራና የምስጋና መንፈስ ይላበሳሉ።
የዛሬው የመኸር ወቅት ከቀደሙት ዓመታት የተለየ ትርጉምና ሀገራዊ ተልእኮ ይዞ መጥቷል። ይህ ወቅት የምግብ እጥረትና ጥገኝነትን በማስወገድ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የሀገርን ክብርን የመመለስ አዲስ የታሪክ ምእራፍ መነሻ ሆኗል። የመኸር ወቅት ሲጠባ ከሰማይ የሚወርደው የክረምት ደመና አልፎ አየሩ መለስ ይላል፤ ፀሐይ በደማቅ ብርሃኗ መስኩን ታበራለች። ክረምቱን ሙሉ በዝናብና በጭቃ ውስጥ ደክሞ፣ ዘርቶና አለስልሶ ያሳደገው አርሶ አደር የድካሙን ፍሬ ለማየት አይኖቹ ወደ ማሳው ያማትራሉ።
በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የመኸር አዝመራ የሥራ ወቅትን ብቻ ሳይሆን የማህበረሰባዊ ትስስርን ያመለክታል። በማለዳ ከወፎች ጫጫታ ጋር የሚነቃው አርሶ አደር ማገዶውንና ማጨጃውን ይዞ ይሰማራል። በአብዛኛው ወንዶች በማጨድ፤ ሴቶችና ህፃናት ደግሞ የታጨደውን ሰብል በስርዓት በማሰርና በመከመር ይተባበራሉ። ይህ የመደመር፣ የህብረትና የደቦ አሰራር የኢትዮጵያውያን የወል ጥበብና የመረዳዳት እሴት መግለጫ ነው።
በመኸር ወቅት ትልቁ ፈተና እና ትኩረት ሰብልን ወቅቱን ጠብቆና በጥንቃቄ መሰብሰብ ነው። የመኸር አዝመራ በሰዓቱ ካልተሰበሰበ ያልተጠበቀ ዝናብ መና ሊያስቀረው ይችላል። በመሆኑም አርሶ አደሮች ጊዜ ሳይሰጡ አዝመራቸውን በፍጥነትና በብቃት ለመሰብሰብ ሌሊትና ቀን ይሰራሉ። አዝመራን ያለብክነት መሰብሰብ የምርት ጥራትን ጠብቆ ወደ ጎተራና ወደ ገበያ ለማድረስ ወሳኝ ነው።
የሰብል ምርት ከማጨድ እስከ ጎተራ ገቢ እስከሚሆን ድረስ የሚደረግ የጥራትና የፅዳት ጥንቃቄ፣ በድካም የተገኘውን ምርት ከብልሽትና ከብክነት ይከላከላል። ይህም የአርሶ አደሩን የብዙ ወራት ላብና ሀገራዊ ሀብትን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ያስችላል። በመሆኑም አሁን ላይ በዘመናዊ ማሽነሪዎች (ኮምባይነር ሃርቨስተር) ሰብልን የመሰብሰብ ልምድ እያደገ በመሄዱ ሲታጨድም ይሁን ሲወቃ ብክነትን ማስቀረት አስችሏል።
በኢትዮጵያ ግብርና ልማት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተው የስንዴ ልማትና ምርታማነት መሆኑ ይታወቃል። የበጋ መስኖን ጨምሮ በመደበኛ ወቅቶች ስንዴን በስፋት በማምረት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል። በዚህም ምርታማነትን የማሳደግና ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ስኬታማ እየሆነ ይገኛል።
የስንዴ ምርት መጠን ከፍተኛ ማንሰራራት በማሳየቱ የዜጎች የምግብ ዋስትና መሰረት ከመሆን አልፎ የጎረቤት አገራትም ሲሳይ ሆኗል። በመሆኑም ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የእህል ጎተራ የማድረግ ርዕይ እውን እያደረገ ይገኛል። ለዘመናት "የረሃብና የእርዳታ እጅ ዘርጊ" ተደርጋ ትታይ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ አምርታ በምግብ ፍጆታ ራሷን የምትመግብ መሆኑን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
በምግብ ራስን መቻል ማለት የሀገርን ነፃነትና ክብር ማስከበር ነው። በእርዳታ እህል ላይ የነበረውን ጥገኝነት በማስቀረት ሀገራዊ ሰብዓዊ ክብርና ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል። የታጨደው ሰብል ተወቅቶ ወደ ጎተራ ሲገባ፤ ከአርሶ አደሩ አልፎ በከተሞች የምርት አቅርቦት ሲበራከት የገበያ መረጋጋትና የምግብ ዋስትና መሰረት እየተጠናከረ ይሄዳል። ለዚህም ነው የመኸር በረከት፤ የምግብ ሉዓላዊነት መሰረት የሚሆነው።
የምርት ማደግና ሰብልን ያለብክነት መሰብሰብ ቀጥታ ወደ የቤተሰብ ብልጽግና ይተረጎማል። አርሶ አደሩ ምርቱን ለራሱ ከተጠቀመ በኋላ ትርፉን ለገበያ በማቅረብ፡ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፣ የልጆቹን ትምህርትና ጤና ያሟላል። የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ኢንቨስትመንቶችን ለመስራት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ይፈጥራል። ገጠሩ ክፍል ከዕለት ጉርስ ፍለጋ ወጥቶ ወደ ሀብት ፈጣሪነትና ወደ አጠቃላይ ብልጽግና ይሸጋገራል።
በመሆኑም የመኸር ወቅት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ፅናት፣ የላብና የህብረት ጥረታቸው በውጤት የሚደመደምበት ወርቃማ ጊዜ ነው።