ቀጥታ፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል - ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) 

ሆሳዕና፤ ጥቅምት19/2019(ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለፁ።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ባካሄደው 50ኛ መደበኛ ስብሰባ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪው ሩብ ዓመት የክልሉ መንግስት የዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በከተማና በገጠር የመሰረት ልማት ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉና የሚያዘምኑ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።

በኮሪደር ልማት ከተሞችን ለኑሮና ለሥራ ምቹ የማድረግ፤ በገጠር ኮሪደር ልማት ደግሞ የአርሶ አደሩን አኗኗር የማሻሻልና የመለወጥ ተግባራት ውጤት የተገኘባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ከበልግና ከመኸር ወቅት በተጨማሪ በበጋ በመስኖ እንዲያለማ መደረጉን ገልጸዋል።


 

በዚህም የገቢ አቅሙን ለማሳደግና ገበያን ለማረጋጋት ያስቻሉ ሥራዎች በሩብ ዓመቱ መከናወናቸውን ነው የገለጹት።

ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን በተያዘው ዕቅድ መሰረት የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎችም ተጨባጭ ስኬት ለማስመዝገብ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ  ተናግረዋል።

በመደመር መንግሥት አፈጻጸም ከቁጥር ይልቅ መሬት ላይ በተጨባጭ በተመዘገቡ ስኬቶች እንደሚለካ ገልጸው፣ በዚህም በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ሁሉንም አቅም በማሰባሰብ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መስራት እንደሚገባ ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለዚህም ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም