ቀጥታ፡

የሳይበር ደኅንነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልካም ስምና የደንበኞች እምነት መሰረት ነው - አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፦ የሳይበር ደኅንነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልካም ስምና የደንበኞች እምነት መሰረት መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ 

ባንኩ 3ኛውን የሳይበር ደኅንነት ወር ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል። 


 

በጉባኤው ማስጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የባንኩ ዋነኛ የአገልግሎት ምርት የሕዝብ እምነት መሆኑን ገልጸዋል። 

የባንኩን ደንበኞች እምነት አስጠብቆ ለማስቀጠልም የገንዘብና የመረጃ ደኅንነት አስተማማኝነትን በማስጠበቅ ሁሉም አመራርና ሠራተኞች የጋራ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል። 

በዲጂታል ዓለም ውስጥ እምነት የደንበኞች ገንዘብና የመረጃ ደኅንነት መጠበቅ ወሳኝ ነው ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትክክለኛ ግብይቶችም ተግባራዊ ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል። 

የሳይበር ደኅንነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልካም ስምና የደንበኞች እምነት መሰረት እንደሆነ አስገንዝበዋል። 

የሳይበር ደኅንነት አጥቂዎች ከባንኩ የመጡ የሚመስሉ የስልክ ጥሪዎችንና መልዕክቶችን ለደንበኞች በመላክ እንደሚያታልሉ አስገንዝበዋል። 


 

ለአብነትም የደንበኞችን የይለፍ ቃል፣ የአንድ ጊዜ ማረጋገጫ ኮድ (OTP) እና ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለማግኘት እንደሚሞክሩም አስረድተዋል። 

ለዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቴክኖሎጂዎችን በሳይበር ደኅንነት በመጠበቅ የደንበኞችን እምነት ማስቀጠል የሚችል ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሁሉም ደንበኞች እኩል የቴክኖሎጂ እውቀትና የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ ስለሌላቸው የግንዛቤ ሥራውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። 

የባንኩ ሠራተኞች የሳይበር ጥቃት መከላከያ ሰንሰለቱ አካል ናቸው ያሉት አቤ ሳኖ፤ የሳይበር ጥቃቶችም የሰውን ስህተትና የእምነት ግንኙነት ለመፈተን የሚሞከሩ ሙከራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። 

በዚህም የባንኩ ሠራተኞች የደንበኞችን ገንዘብና ሚስጥራዊ መረጃ መጠበቅ አለፍ ሲልም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

የደንበኞችን ግንዛቤም በየጊዜው በማሳደግ በቀጣይነት ያለው ሥራ መስራት እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ ከመመከት ይልቅ ከመፈጸማቸው በፊት ለመለየትና ለመከላከል እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ምክትል ፕሬዚዳንት አማረ አሰፋ በበኩላቸው፤ የሳይበር ስጋቶችን በመከላከል የደንበኞችን እምነት የሚያጠናክር አስተማማኝ የቴክኖሎጂ ደኅንነት ሥርዓት እየዘረጋ ነው ብለዋል። 

የንግድ ባንክ የዲጂታል ግብይት ከ92 በመቶ በላይ መድረሱን እና ይህንን ዕድገትም በአስተማማኝ የደኅንነት ሥርዓት በመደገፍ የደንበኞችን መረጃና ገንዘብ በመጠበቅ የደንበኞችን እምነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። 


 

የኢትዮጵያን ቁልፍ መሰረተ ልማቶች በመጠበቅ የሳይበር ደኅንነት ስጋቶችን ማክሸፍ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ተፈጥሯል ያሉት ደግሞ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን አሹራንስ ዘርፍ ተወካይ ጥላሁን እጅጉ (ዶ/ር) ናቸው። 

ለዚህም በ24/7 የሥራ ቁርጠኝነት በቁልፍ መሰረተ ልማት የሳይበር ደኅንነት ጥበቃ አስተማማኝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 

3ኛውን የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ ወር ኮንፈረንስ እና አውደ ርዕይ በፋይናንስና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የደኅንነት ግንዛቤን፣ ዝግጁነትንና ትብብርን ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም