ቀጥታ፡

ከሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተናል

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፡-የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተንዛዛ የቢሮክራሲ አሰራርና  የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ለሙስና የተጋለጡ አሰራሮችን ከማስቀረት ባለፈ የመንግስት አገልግሎትን በፍትሀዊነት እንዲያገኙ መንገድ ማበጀቱንም ገልፀዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል ተገልጋዮች እንዳሉት ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠቱ ቀደም ሲል ሲገጥማቸው የነበረውን የጊዜ ብክነትና እንግልት አስቀርቷል።


 

የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ባለንብረት የሆኑት አቶ ባህሩ ፀጋዬ፤ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ እንደመጡ ጠቅሰው፣ በማዕከሉም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ባለመኖሩ የጊዜ ብክነትና እንግልት ይገጥማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በማዕከሉ  ይህ ችግር ተፈትቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ባህሩ እንዳሉት በማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል አሰራር መዘርጋቱ ሁሉንም መረጃዎች በቅጽበት ለማግኘት ከማስቻሉ ባለፈ ከዚህ በፊት ፋይል ጠፍቷል እየተባለ ለምልልስ ስንዳረግበት የነበረውን አሰራር አስቀርቷል ብለዋል።


 

ለኢሚግሬሽን አገልግሎት ከነገሌ አርሲ ወደ ሀዋሳ መምጣቷን የተናገረችው ወይዘሪት ንጋት ወልደፃድቅ በበኩሏ፣  ከዚህ በፊት እስከ ስምትን ወር ይፈጅባት የነበረን የፓስፖርት ዕድሳት በማዕከሉ በተቀላጠፈ ሁኔታ ማግኘቷን ትናግራለች፡፡

የፓስፖርት መረጃዎችዋን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰርና ሌሎች አገልግሎቶችን በፍጥነት ማግኘቷ እርካታን እንደፈጠረላት ተናግራለች።

አርቲስት አስቻለው ቢርቦ በበኩሉ ለአሻራ አገልግሎት ወደ ማዕከሉ መምጣቱን ገልፆ፣ ቀልጣፋ አገልግሎቱ ጊዜያችንን ብቻ ሳይሆን ወጪንም ለመቆጠብ አስችሎናል ብሏል፡፡


 

መንግሥት ለዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያሳየውን ቁርጠኝነት ያደነቀው አርቲስት አስቻለው፣ ከዚህ በፊት የነበሩ ለሙስና የተጋለጡ አሰራሮችን የሚያስቀር ሥርዐት በመዘርጋቱ እጅግ መደሰቱን ተናግሯል፡፡

የሲዳማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንግዳየሁ ዘውዴ፤ ከዚህ በፊት የነበረው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሰው ተኮር ባለመሆኑ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል።


 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ የዜጎችን እርካታና አመኔታ ማረጋገጥ የተቻለባቸው አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው ብለዋል፡፡

በማዕከላቱ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከ12 ወደ 24 ማሳደግ ሲቻል የአገልግሎት አይነቶች ደግሞ ከ38 ወደ 98 ከፍ ማለታቸውን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ከተጀመረበት ከመስከረም 2018 ጀምሮ እስካሁን በሁለት ማዕከላት ለ141 ሺህ 823 ዜጎች አገልግሎት ለመስጠት መቻሉም ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም