ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል የምርምር ሥራዎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል የምርምር ሥራዎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው
ጎንደር፣ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ):- ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል የምርምር ሥራዎች የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን አርሶ አደር የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሀላፊ መምህር ተሾመ ሙሏለም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር የተጣጣመ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ምርምር እያካሄደ ነው።
ለእዚህም በሰሜን ተራሮች አካባቢ የሚገኘው ደጋማና ውርጭ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ ከፍተኛ የሥጋ ምርት የሚሰጥ አውራ በግ ላይ ምርምር በማካሄድ ለማህበረሰቡ ማቅረቡን ተናግረዋል።
ይህም ማህበረሰቡ በተለምዶ ከሚያረባቸው አነስተኛ ሥጋ ካላቸው በጎች ተላቆ የተሻለ ክብደትና ቁመና ያላቸውን በጎች በማርባት ዘላቂ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያስችል የምርምር ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ምርምር ውጤት የሥጋ ጥራት፣ ጣዕምና ንጥረ ነገሮች ላይ መሰረተ ያደረገ በመሆኑ እንስሳቱ በገበያ ተፈላጊ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከበግ ዝርያ ማሻሻል ጎን ለጎን ባካባቢው ያሉ ወጣቶች በዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ የወተት ላም፣ የስናር አህያ እና የኮርማ በሬ ዝርያ ማሻሻል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን የእንስሳትና አሣ ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸጋው ጌታቸው በበኩላቸው እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
ከልማት ሥራዎቹ መካከል በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በደሮ እርባታ እና በንብ ሀብት ልማት ሥራዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በምርምር የወጡና የተሻለ ዝርያ ያላቸውን 20 የሰሜን አውራ በጎች በሁለት ወረዳዎች በማሰራጨት የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ ቁጥራቸውን ከ2 ሺህ በላይ በማድረስ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የደባርቅ ከተማ ነዋሪ አቶ ንጉስ ፀጋው የተሻሻሉ የአውራ በግ ዝርያዎችን በማርባት ክብደታቸው የተሻለና ተፈላጊ የሆኑ በጎችን ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
በምርምር የተሻሻሉ የሰሜን አውራ በግ ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ምህረቴ አዳነም የበግ ዝርያዎቹ ከተለመዱት ነባር የአካባቢው የበግ ዝርያዎች በመልክ፣ በቁመት እና በክብደት የተሻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።