ቀጥታ፡

የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሰቆጣ፣ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፡-በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የተገነባው የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሰይፈ ሞገስ እንደገለጹት፣ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ፈጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።


 

የተማሪዎች ማደሪያ፣ መማሪያና ሌሎች መገልገያ ህንፃዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆናቸው በህዳር ወር ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎች መመደባቸውን ጠቁመው፣ ርዕሰ መምህር ከመመደብ ባሻገር የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅጥር እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


 

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ወደ ስራ መግባት ብቁ ተማሪዎችን ከማፍራት ባለፈ፣ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ ተማሪዎችን የሚያነቃቃና የተወዳዳሪነት መንፈስን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሆነው የተመደቡት አቶ ደሳለኝ ጌታወይ እንደገለጹት፣ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። 


 

የመምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቅጥር ከመፈጸም ጎን ለጎን፣ የተማሪዎች መገልገያና ሌሎች ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በሰቆጣ የዋግ ሥዩም አድማሱ ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አዝመራ ጣምተው እንደገለጸችው፣ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ስራ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉ ለተማሪዎች ትልቅ ተስፋን የሚሰንቅ ነው። 

በአካባቢያችን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መኖሩ የተማሪዎችን ተፎካካሪነትና ተወዳዳሪነት መንፈስ የሚያሳድግ ነው ያለችው ተማሪዋ፣ ለዚህም ጠንክረን እንሰራለን ብላለች።

የሰቆጣ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በክልሉ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የበጀት ድጋፍ የተከናወነ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም