ቀጥታ፡

በመዲናዋ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ የሚገኙት የገበያ ማዕከላት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የገበያ ማዕከላት ጥራት ያላቸውን የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እያስቻሏቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ፣ ገበያውን ለማረጋጋት እና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ሕብረተሰብ ለመደገፍ በከተማ አስተዳደሩ እና በባለድርሻ አካላት በርካታ የተቀናጁ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላትን በመገንባት ሸማቹ የግብርና ምርቶችን በአካባቢውና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እያስቻሉ ነው።

ኢዜአ በለሚ ኩራ እና በሰሚት የግብርና ምርቶች ማዕከላት በመገኘት ያነጋገራቸው ሸማቾችና አምራቾች የገበያ ማዕከላቱ ያነጋገራቸው ሸማቾችም ይህንን አረጋግጠዋል።

በሰሚት የገበያ ማዕከል ስትገበያይ ያገኘናት ሸማቾች መካከል አበባ ሳሙኤል፤ ማዕከሉ በአቅራቢያቸው መከፈቱ ሁሉንም ዓይነት አትክልትና ፍራፍሬ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እንዳስቻላት ገልጻለች፡፡


 

በለሚ ኩራ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ሲገበያይ ያገኘነው በኩረ ባዩ በበኩሉ፤ መንግሥት በየአቅራቢያቸው ባስገነባቸው ማዕከላት አትክልት፣ ፍራፍሬና የሰብል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት መቻላቸው ለእነሱ ትልቅ እፎይታ መስጠቱን ተናግሯል።

በማዕከላቱ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ አምራቾች በበኩላቸው፤ ማዕከላቱ የደላላ ጣልቃ ገብነትንና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ምርታቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው ማቅረብ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።


 

ከአምራቾች መካከል ሙሉጌታ አያና፤ የገበያ ማዕከላቱ መኖራቸው ምርቶችን ያለምንም ተላላኪ በቀጥታ ለሸማቹ ለማድረስ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ አምራች ማርታ መኳንንት ደግሞ የደላላ ጣልቃ ገብነት በመቀረሱ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ ለማቅረብ ማስቻሉን አስረድተዋል።


 

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋትና የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ምርቶች ከክልሎች በቀጥታ ከአምራቹ ያለምንም ደላላ ጣልቃ ገብነት በመዲናዋ በተገነቡት ማዕከላት በኩል ለሽያጭ እንዲቀርቡ በማድረግ ሸማቹ ተጠቃሚ እንዲሆን ቢሮው በቀን 24 ሰዓት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


 

ማዕከላቱ ምርት በስፋትና በጥራት እንዲቀርብ በማድረግ የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት እንዲፈጠር ማስቻላቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ በቀጣይም መሰል የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም