ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጽኑ ሉዓላዊነትና የቀጣናው ዋስትና- ዘመናዊ ጄቶች የታጠቀው አየር ኃይል

በለይኩን አሰፋ    

ትልቅ ሕዝብ፣ትልቅ ሀገርና ታላቅ ራዕይ      

ሰማይ ወሰን የሌለው የተፈጥሮ ስፋት ቢሆንም፣ ለአንድ ሀገር ግን የሉዓላዊነት፣ የደኅንነትና የብሔራዊ ጥቅም አካል ነው። በዚህ ሰማይ ላይ የሀገርን ክብር ለመጠበቅ፣ የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥና የውጭ ስጋቶችን ለመከላከል የቆመው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገሪቱ የመከላከያ ሥርዓት ወሳኝ አካል ነው። 

አንድ ሀገር ሉዓላዊነቷን በምድር ላይ ብቻ አትጠብቅም። የአየር ጠፈሯን መጠበቅ፣ ከድንበሯ በላይ የሚንቀሳቀሱ ስጋቶችን መከታተልና ለሀገራዊ ደኅንነት የሚያስፈልገውን የአየር የበላይነት ማረጋገጥ የዘመናዊ መከላከያ አቅም ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ የብሔራዊ ደኅንነት ምሰሶ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱ የሆነ ታሪክ፣ የተለየ ተልዕኮና የረጅም ዘመን የአገልግሎት ልምድ አለው።

ከታሪካዊ አመሠራረቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአውሮፕላኖችና ከወታደራዊ መሣሪያዎች የበለጠ ትርጉም ይዞ ቆይቷል። ከጀግንነት፣ ከሙያዊ ብቃትና ከሀገር ፍቅር መርህ ጋር የተያያዘ ተቋም ሆኖ በተለያዩ ዘመናት የሀገሪቱን የአየር ደኅንነት ለማስጠበቅ ተልዕኮውን ተወጥቷል። የዚህ ተቋም ታሪክ የሚዘከረው በተከናወኑ ዘመቻዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገር ጥቅም በተከፈሉ መሥዋዕትነቶች፣ በተገነባው ሙያዊ ልምድና ከትውልድ ወደ ትውልድ በተላለፈው የአገልግሎት መንፈስ ጭምር ነው።

ዛሬ የዓለም ወታደራዊ አሠራር በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት ወቅት፣ የአየር ኃይል አቅም በአውሮፕላኖች ብዛት ብቻ አይለካም። የራዳርና የክትትል ሥርዓቶች፣ የመረጃ ልውውጥ፣ የአየር መከላከያ፣ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ የጥገናና የቴክኒክ ብቃት እንዲሁም የተቀናጀ የውጊያ አሠራር የአቅሙ ወሳኝ መለኪያዎች ሆነዋል። 

ታዲያ የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በየጊዜው ከሚለዋወጡት ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ እና የቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር አብሮ በመጓዝ አሁን ላይ ሰፊና ጥልቅ የሆነ የዘመናዊነት ሽግግር እያደረገ ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተካሄደው ሀገራዊ የሪፎርም ሂደት፣ ለአየር ኃይሉ መሰረታዊ የላቀ ጥንካሬ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። የመደመር መንግሥት ለአየር ኃይሉ መጠናከር እያበረከተ ያለው የቴክኖሎጂ፣ የመሰረተ ልማት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ግንባታ ድጋፍ ተቋሙን በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ዘመናዊ የጦር ኃይል አድርጎታል።

የአየር ኃይሉ የዘመናዊነት ጉዞ ዋነኛው መገለጫ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መታጠቁ ነው። ተቋሙ ወቅታዊ የጦርነት ስልቶችን መሠረት ያደረጉ ዘመናዊ ሲስተም የታጠቁ ድሮኖችን በስፋት በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም የቅድመ-ማስጠንቀቂያ እና ተፈላጊውን ኢላማ የመምታት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። ከዚህም በተጨማሪ ነባር የውጊያ አውሮፕላኖችን እና ሄሊኮፕተሮችን ማዘመን ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ የላቁ የውጊያ አውሮፕላኖችን መታጠቁ የአየር ክልል የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ አስችሎታል። 

ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ዛሬ ከሩሲያ የተረከበችው የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ተጠቃሽ ናቸው። ይህም የኢትየጵያን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሌላ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት በሩሲያ ተገኝተው የጦር ጄቶችን በተረከቡበት ወቅት  ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይሏ እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያላበሳት ይገኛል ብለዋል።

እነዚህን እጅግ ዘመናዊ የጦር ጄቶች በመታጠቅ ብቻ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ መሆን ችላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ስኬት አስመልክተው ሲናገሩም፦

"ይህ ታሪካዊ ስኬት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ ወደፊትም የጋራ ደህንነታችንን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድንቀጥል ትልቅ አቅም ይሆነናል።" ብለዋል።

በዚህ ድንቅ ዕምርታ የታጀበው የአየር ኃይላችን ዝግጁነት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን ይህ ታሪካዊ ቀን በግልጽ አሳይቷል።

ይህ ሀገራችንን የሰማይ ላይ ጥበቃ (Air Defense) ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ትልቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው። ሱ-35 በአየር ላይ የሚደረጉ ውጊያዎችን በመቆጣጠር፣ የጠላት አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን በረጅም ርቀት ላይ የማወቅ፣ የራዳር ሥርዓቶችን የማደናቀፍ እና የማስወገድ ከፍተኛ ብቃት ያለው ሲሆን፤ አየር ኃይሉ ቀደም ሲል ከታጠቃቸው Su-30፣ Su-27 እና ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ጋር የተቀናጀ የሰማይ ጥበቃ መረብ ለመፍጠር ያስችላል።

የማንኛውም አየር ኃይል ጥንካሬ መሠረቱ የቴክኖሎጂው ጥራት ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይሉ ብቃት ነው። ለዚህም ስኬት አጋዥ እንዲሆን የበረራ ባለሙያዎችን፣ የቴክኒክ እና የምህንድስና ባለሙያዎችን የሚያሰለጥንበት አካዳሚ በዘመናዊ የበረራ ልምምድ መሳሪያዎች (Flight Simulators) እና ላቦራቶሪዎች እንዲደራጅ ተደርጓል። ፓይለቶች እና የጥገና ባለሙያዎች ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ እና የስልት ደረጃ ጠብቀው እንዲሰለጥኑ በመደረጉ በከፍተኛ ደረጃ ፕሮፌሽናል የሆነ የሰው ኃይል መገንባት ተችሏል።

ዛሬ ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚደረገው ሽግግር የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እና የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናንም ያካተተ ነው። ቢሾፍቱን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የአየር ኃይል ጣቢያዎች በዘመናዊ መገናኛዎች፣ የበረራ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች እና የደህንነት ሥርዓቶች እንዲደራጁ ተደርገዋል። የመረጃ ልውውጥን እና የዕዝ ሥራዎችን በዲጂታል መንገድ የሚያቀናጁ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶችንም መዘርጋት ተችሏል።

ከዚህ ባሻገርም ኢትዮጵያ በኤሮስፔስ እና በመከላከያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በሀገር ውስጥ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ማምረት እና መገጣጠም መጀመሯ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። እንደ ኤሮ ዓባይ (Aero Abay) እና ስካይ ዊን (Sky Win Aeronautics) ያሉ የድሮን ማምረቻ ፋብሪካዎች እውን መሆን ሀገሪቷ ከውጭ ጥገኝነት ወጥታ የራሷን የቴክኖሎጂ አቅም እንድትገነባ መንገድ ከፍቷል። ፋብሪካዎቹ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የሚመሩ በመሆናቸው ለከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ መደላደል የፈጠሩ ሲሆን፤ ለስለላ፣ መረጃ ለመሰብሰብ፣ ተፈላጊውን ዒላማ ነጥሎ ውጤታማ እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም ለስልታዊ ወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖችን በማምረት ላይ ናቸው። እነዚህ የሀገር ውስጥ ውጤቶች የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ በዘመናዊ ግብርና፣ በሜጋ ፕሮጀክቶች ጂኦስፓሻል ክትትል፣ በተፈጥሮ አደጋዎች የጉዳት መጠን ዳሰሳ እና በአስቸኳይ የህክምና ቁሳቁሶች ማድረስ ላይ ከፍተኛ ሲቪል አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥንካሬ የአገራችንን ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ዋስትና ነው። ሱ-35 አውሮፕላኖች እና ዘመናዊ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች መታጠቁ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሀገራዊ የኢኮኖሚ፣ የኃይል እና የሎጂስቲክስ ማዕከላትን ከአየር ላይ ስጋቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ያስችላል። በወታደራዊ ስትራቴጂ ውስጥ ጥንካሬን ማሳየት ራሱ ግጭቶችን የመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ የላቀ የአየር የበላይነት አቅም መገንባቷ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሊነሱ የሚችሉ ስጋቶችን በቅድሚያ ለመከላከል የማይደፈር አቅም ይሆናሉ።

ይህ ጠንካራ የመከላከል አቅም መኖሩ ኢትዮጵያ በቀጣናው የደህንነት እንቅስቃሴዎች ላይ የሰላም እና የመረጋጋት አምባሳደር ሆና እንድትቀጥል የሚያስችላት ሲሆን፤ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወቅትም አስፈላጊውን የአየር ክልል ጥበቃ እና ደህንነት ለመስጠት ከፍተኛ ዝግጁነትን ፈጥሯል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል እያደረገ ያለው የዘመናዊነት ሽግግር የታሪክ አደራውን ከነገው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ያጣመረ ነው። በሰው ኃይል ልማት፣ በሀገር ውስጥ የድሮን ማምረቻዎች፣ በዘመናዊ የሱ-35 የውጊያ አውሮፕላኖች ትጥቅ እና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ላይ የተደረጉት ተጨባጭ ለውጦች ተቋሙን በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ካሉ ጠንካራ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የአየር ኃይሎች አንዱ አድርገውታል። ይህ ጉዞ የኢትዮጵያን ሰማይ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ እና ለአካባቢው ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ስትራቴጂካዊ ምሽግ ሆኗል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም