በትግራይ ክልል በተዋረድ በሚዋቀሩ የሕዝብ አስተዳደር ተግባራት የሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚያሳልጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በተዋረድ በሚዋቀሩ የሕዝብ አስተዳደር ተግባራት የሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚያሳልጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል በተዋረድ በሚዋቀሩ የህዝብ አስተዳደር ተግባራት የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚያሳልጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑን በክልሉ የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር አስታወቀ።
የህገ ወጡ የህወሐት ቡድን በትግራይ ህዝብ ስም እየነገደ "እኔ ካልመራሁት" በሚል በተደጋጋሚ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ ይታወቃል።
ቡድኑ በየደረጃው የነበሩ የመንግስት ተቋማትን በማፍረስ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጡ በማድረግ ህዝቡ ለከፍተኛ እንግልትና ለስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዲጋለጥ አድርጓል።
በክልሉ ሰላም እንዲጸና፣ የሕዝቡ ስነ ልቡና እንዲስተካከል፣ ወደ ልማትና የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ዝግጁነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ በየደረጃው የሕዝብ መድረኮችን የማዘጋጀትና ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፍጠርን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ለማከናወን ሀላፊነት የተሰጠው የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር ስራ መጀመሩ ይታወቃል።
በባለአደራ አስተዳደሩ የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተዋረድ በሚዋቀሩ የሚኮኖሚና መልሶ ግንባታ የህዝብ አስተዳደር ተግባራት የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚያሳልጥ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አካባቢያዊ እና ህዝባዊ ጊዜያዊ አስተዳዳሪዎች ማቋቋምና ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር እየተከናወነ ያለው ተግባር ትልቅ አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታችኛውን የመንግስት መዋቅር በጊዜያዊነት የሚያስተዳድሩ አመራሮች በመምረጥ የፈረሱ መዋቅሮች መልሶ የመዘርጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዋና አስፈጻሚው ቴዎድሮስ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተቀሩ አካባቢዎችም በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ እና ፍጹም ዲሞክራሲና ግልጽነት ባለው አሰራር ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ይከበራል ብለዋል፡፡
ባለአደራው አስተዳደር ሲቋቋም ከህዝብና ባለድርሻ አካላት በመተባበር በቀጣይ ስድስት ወራት እንዲሰሩ የተሰጡት ተግባራት ውጤታማ ማድረግ ነው ያሉት ዋና አስፈጻሚው ቴዎድሮስ (ዶ/ር)፤ ሰላም ለማጽናት ከህዝብ መምከር እና የፈረሰ መዋቅር መልሶ መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይነትም በክልሉ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖር እና ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ባለአደራ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡