የጣና ፎረም የባሕር ዳር ከተማን ገጽታ በመገንባትና የቱሪዝም ተጠቃሚነትን በማሳደግ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል - ኢዜአ አማርኛ
የጣና ፎረም የባሕር ዳር ከተማን ገጽታ በመገንባትና የቱሪዝም ተጠቃሚነትን በማሳደግ የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል
ባህርዳር፤ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፡- የጣና ፎረም የባሕር ዳር ከተማን ገጽታ በመገንባትና የቱሪዝም ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ የጎላ አበርክቶ እንደነበረው የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የዘንድሮው የጣና ፎረም ስብሰባ ከወትሮው በተለየ መልኩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የዓለም ዲፕሎማቶች የታደሙበት ነው።
ቀድሞ በተሠራው ሥራ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀልጣፋና ምቹ መስተንግዶ በመስጠት፣ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ከፎረሙ ተሳታፊዎች በተጨማሪ በርካታ ቱሪስቶች በመምጣት በከተማዋ የሚገኙ የተፈጥሮና ታሪካዊ ቦታዎችን መጎብኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።
በፎረሙ ከአፍሪካ መሪዎችና ምሁራን በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች የተሳተፉበት በመሆኑ፣ የአገራችንን ገጽታ በመገንባት ረገድ አበርክቶው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችም ማረፊያቸውን በከተማዋ በሚገኙ ሆቴሎች በማድረጋቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደተቻለም አመልክተዋል።
በከተማዋ የሚገኙ እንደ ጣናና ዓባይ ወንዝ ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎች፣ እንዲሁም አዲሱ የዓባይ ድልድይ፣ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ እስከ አምስት ቀን ድረስ እንዲያራዝሙ ማስቻሉም ተመልክቷል።
የፎረሙ ተሳታፊ የአፍሪካ መሪዎችም በከተማዋ የተገነባውን የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መጎብኘታቸው ለዚህ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴኔጋል አቻው ጋር ጨዋታ ማድረጉን ገልጸው፣ በቀጣይም ስታዲየሙ ተጨማሪ የስፖርት ውድድሮችን የማካሄድ አቅም እንዳለውም ማስገንዘብ ተችሏል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ወጣት አቤል ምስጋናው እና ወጣት ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው ከተማዋ የጣና ፎረም እንግዶቿን በአግባቡ ተቀብላ አስተናግዳ በመሸኘቷ መደሰታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ከተማዋ የበርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ባለቤት በመሆኗ የጎብኚዎችን ቀልብ እንድትስብ አድርጓታል ብለዋል።
ለፎረሙ የመጡ እንግዶችና ሌሎች ቱሪስቶች ከአነስተኛ እስከ ትላልቅ የአገልግሎት ተቋማትን ተጠቃሚ እንዳደረጉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የአፍሪካ መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎችን በማሳተፍ ከጥቅምት 13 እስከ 15 ቀን 2019 ዓ.ም የተካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም በስኬት መጠናቀቁ ይታወቃል።