ኢትዮጵያና አትሌቲክስ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና አትሌቲክስ
አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ ከስፖርት በላይ ነው። የሀገር ኩራት፣ በዓለም አደባባይ በተደጋጋሚ ስሟ የሚጠራበትና የዜጎቿ የደስታ ምንጭ ነው። ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ዓለምን በመምራት የምትታወቅ ሀገር ስትሆን፣ የአትሌቶቿ ድል ከሜዳልያ ባለፈ የከፍታዋ ማሳያ ነው። ሰንደቅ አላማዋ በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና መድረኮች ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ኢትዮጵያውያን በክብርና ኩራት በደስታ ሀሴት ይሞላሉ።
የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ታሪክ በዓለም መድረክ ጎልቶ መታየት የጀመረው በ1952 ዓ.ም. በሮም ኦሊምፒክ ነው። አበበ ቢቂላ በማራቶን በባዶ እግሩን ሮጦ የወርቅ ሜዳልያ በማጥለቅ ከጥቁር አፍሪካዊያን የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን ታሪክ ሰርቷል። በ1956 ዓ.ም. በቶኪዮ ኦሊምፒክም ማራቶንን በድጋሚ በማሸነፍ ሁለት ጊዜ በተከታታይ የወርቅ ሜዳልያ ያሸነፈ የመጀመሪያው አትሌትም ነው። ከእርሱ ድል በኋላም ማሞ ወልዴ፣ ምሩጽ ይፍጠርና ሌሎችም ጀግኖች ድል አድራጊነትን አስቀጥለው ለትውልድ አስተላልፈዋል።
በመቀጠልም ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስህን፣ ገዛኸኝ አበራ እና ሌሎችም አትሌቶች በትራክና በአገር አቋራጭ ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል። ኃይሌና ቀነኒሳ በ10,000 ሜትር ያደረጉት ፉክክር የስፖርት ታሪክ ከማይረሷቸው ትዕይንቶች መካከልም ይጠቀሳል። ደራርቱ ቱሉ በ1984 ዓ.ም. በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር ወርቅ በማግኘት ከጥቁር አፍሪካዊያን አትሌቶች የመጀመሪያዋ የኦሊምፒክ ወርቅ ተሸላሚ ሆናለች።
ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ለምን ስኬታማ ሆነች የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ይነሳል። መልሱ አንድ ምክንያት ብቻ አይደለም። የመጀመሪያው የሀገሪቱ ከፍተኛ ደጋማ መልክዓ ምድር ነው። ከባሕር ጠለል በላይ በከፍተኛ ቦታ መኖርና መሠልጠን የሰውነት የኦክሲጅን አጠቃቀም አቅምን ያሳድጋል። ሁለተኛው ጠንካራ የልምምድ ባህልና የአትሌቶች ጽናት ነው።
በተለይም ታዳጊዎች አንድ ሻምፒዮን የሆነ አትሌት ሲያዩ "እኔም እችላለሁ" የሚል ተስፋ በማሳደርና አርዓያ በማድረግ ወደ ሩጫ በመግባት ብርቱ ተወዳዳሪ ይሆናሉ። እንደ አርሲ በቆጂ ያሉ አካባቢዎች ከትናንሽ መንደሮች ተነስተው ዓለም አቀፍ ኮከቦችን ያፈሩት በዚህ ምክንያት ነው። በተጨማሪም የአትሌቲክስ ክለቦች፣ የትምህርት ቤት ውድድሮችና የአሠልጣኞች ሥራም የራሳቸው ድርሻ አላቸው።
አትሌቲክስ ለብዙ ወጣቶች የሥራና የተስፋ በር ነው። ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚለውጡበት አጋጣሚንም ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት፣ ቱሪዝምንና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
የሀገሪቱን ገፅታ ከሚገነቡ የሀገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ ሩጫ (Great Ethiopian Run) በ1994 ዓ.ም. በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሃሳብ አመንጪነት በአዲስ አበባ የተጀመረ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ነው። በየዓመቱ ኅዳር ወር ላይ በመስቀል አደባባይ ተጀምሮ የሚጠናቀቀው ይህ ውድድር፣ ከአፍሪካ ትልልቅ የጎዳና ላይ ሩጫዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታትም በጥቂቶች የተጀመረው ተሳታፊ ቁጥር ዛሬ ላይ በአስር ሺዎች የሚሳተፉበት ሆኗል። የውጭ አገራት አትሌቶች፣ አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች፣ ተማሪዎች፣ ሠራተኞች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ በአንድነት ይሮጣሉ።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስኬት ከስፖርታዊ ፋይዳው ባሻገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታንም እያተረፈ ይገኛል። ውድድሩ ለተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራዊ ዓላማዎች ድጋፍ የሚሰበሰብበት መድረክም ሆኗል፤ ጤናማ አኗኗርንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ለማስፋፋትም አግዟል። ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎችንና ጎብኚዎችን በመሳብ ለቱሪዝምና ለሀገር ገጽታ ግንባታም አስተዋጽኦ አድርጓል። በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም ተመሳሳይ ሩጫዎች እንዲዘጋጁ መነሻ በመሆን አዳዲስ አትሌቶች እንዲፈጠሩም መሰረት እያኖረ ይገኛል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያና አትሌቲክስ የማይለያዩ የኩራትና የተስፋ ምልክት በመሆኑ ዘልቀዋል። ከአበበ ቢቂላ ጨምሮ እስከ የዛሬዎቹ ኮከቦች ድረስ ያለው የአሸናፊነት ቅብብሎሽም ተጠናክሮ ቀጥሏል። አትሌቲክስ ከተደገፈ የኢትዮጵያ የገር ዲፕሎማሲ (soft power diplomacy) መሰረት ሆኖ ይቀጥላል።