ቀጥታ፡

የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በባለሀብቶች ተሳትፎ ማደግና በውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ስኬት እያስመዘገበ ነው

ሀዋሳ፤ ጥቅምት19/2019 (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በባለሀብቶች ተሳትፎ ማደግና በውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለጸ።

የሀዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ፤ መንግስት ዘርፉን ለማበረታታት ባከናወናቸው ተግባራት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የባለሀብቶች ተሳትፎ ከማደጉ ባለፈ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ሊመዘገብ ችሏል።

ባለፈው ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን በኢኮኖሚ ዞኑ ባደረገው ምልከታ በተለያየ ምክንያት ከሥራ ውጭ የነበሩ ካምፓኒዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጾ ማድረጉን ጠቅሰዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ ዞኑ የጨርቃ ጨርቅ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ የሶላር ፓኔል አምራቾችን ጨምሮ 20 ካምፓኒዎች በማምረት ሥራ ላይ እንሚገኙ ተናግረዋል።

በዚህም ባለፈው በ2018 በጀት ዓመት ከልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት የተለያዩ ምርቶችን በመላክ ከ170 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማስገኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና ተኪ ምርት በማምረት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክህሎት የበቃ ባለሙያ፣ በቂ የሀይል አቅርቦት መኖርና ቆሻሻን አጣርቶ ለተጨማሪ አገልግሎት የሚያውል ዘመናዊ ተክኖሎጂን መጠቀሙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑን ተመራጭ እንዳደረገው አስረድተዋል።

በኢኮኖሚ ዞኑ እየሰሩ ካሉ ካምፓኒዎች መካከል አልባሳትን በማምረት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከሚልኩ መካከል ሲልቨር ስፓርክ አፓሬል ኢትዮጵያ ኩባንያ አንዱ ነው።


 

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ጎፓላ ከርሺና፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ዕድገት የሰጠው ትኩረትና እያደረገ ያለው ክትትልና ድጋፍ ወደልዩ ኢኮኖሚ ዞን እንዲመጡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በሥራውና በውጤቱ ደስተኞች መሆናቸውን የተናገሩት የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ጎፓና ከርሺና፣ በአሁን ወቅት በቀን የሚመረተውን ከ3 ሺህ በላይ አልባሳት ወደ 5 ሺህ ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኩባንያውን ሥራ የሚያቀላጥፍ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸቱም ለውጤታማነታቸው አስተዋጾ ማደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም