ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት የታሪክ፣ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካዊ መስተጋብር ውጤት ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት የታሪክ፣ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካዊ መስተጋብር ውጤት ነው - ምሁራን
ጅማ፣ ጥቅምት 19/2019 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት የታሪክ፣ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካዊ መስተጋብር ውጤት ነው ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ህልውናና የእድገት መሰረት ሆኖ የቆየ ነው።
ሆኖም ግን፣ በሂደት በነበሩ የታሪክ አጋጣሚዎችና በተሸረቡ ሴራዎች ምክንያት ሀገሪቱ ተፈጥሯዊ የባህር በሯን እንድታጣና ሙሉ በሙሉ ባህር አልባ ሀገር እንድትሆን ተደርጋለች።
በአሁኑ ወቅት የመደመር መንግስት ይህንን ታሪካዊ ስህተት ለማረም እና የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የባህር በር ለማስመለስና አማራጭ የባህር በሮችን ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የኢትዮጵያን በፍጥነት እያደገ የመጣ ህዝብና ኢኮኖሚ ለመደገፍ፣ የጋራ ልማትንና ሰላምን በሚያረጋግጥ መንገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ፣ በህጋዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እንደሆነም መንግስት ያሰምርበታል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሐብት ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ ዳውድ ተማም (ዶ/ር) በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ኢትዮጵያ በአዱሊስ ወደብ አማካይነት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጋር የንግድ ግንኙነት እንደነበራት አስታውሰዋል።
የቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ከዓለም አቀፍ ንግድና ከቀጣናዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ወሳኝ የንግድ መስመር ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከርና የባሕር በር ማግኘቷ ለቀጣናዊ ተሳትፎዋ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀይ ባሕር ለዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉት ምሁሩ፤ በአካባቢው የተለያዩ ኃያላን ሀገራት ያላቸው ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎም የቀጣናውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድ ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት ለማጠናከርና የኢኮኖሚ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የባሕር በር ማግኘቷ አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል።
ይህም የባሕር ሕግንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሠረት ባደረገ ሰላማዊ የውይይትና የትብብር ሂደት መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ የወጪ ንግዷ በሌሎች አገራት ወደቦች ጥገኛ እንዲሆን አድርጓታል ብለዋል።
ይህም የባህር በር መዳረሻን የብሔራዊ ደህንነትና የኢኮኖሚ ጉዳይ አድርጎት መቆየቱን አመልክተዋል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ካላት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ አንጻር የባሕር በር ማግኘቷ ለንግድ ግንኙነቷና ለልማቷ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የባሕር በር ማግኘት ለሀገሪቱ የወጪ ንግድ መስፋፋትና የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ ከሚኖረው ጥቅም ባለፈ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች የልማት ዘርፎች ለሚደረጉ ሥራዎች ተጨማሪ አቅም ሊፈጥር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ፣ የቀይ ባሕር ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥቅም፣ ከንግድ ግንኙነቷና ከቀጣናዊ ሚናዋ ጋር የተያያዘ መሆኑን ምሁራኑ አመልክተዋል።