ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ካልተጠበቀ ዝናብ ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ ነው

ደብረ ብርሃን፣ ጥቅምት 19/2019(ኢዜአ)፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖችንና ባህላዊውን የደቦ አሰራር በመጠቀም ፈጥኖ የመሰብሰብ  ስራ እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ ሁሉም ታየ ዘነበ ለኢዜአ እንደገለጹት ለያዝነው የመኸር ምርት ዘመን በዞኑ 563ሺህ 282  ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።

 ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ እንዲሰበስብ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

እስካሁን በተደረገው ጥረትም በ75ሺህ 525 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የደረሰ ሰብልን በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖችና ደቦን በመጠቀም መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

 በቀጣይም አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብላቸውን ፈጥነው በመሰብሰብ ወደ ጎተራ በማስገባት የምርት ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እንዲሰሩ አቅጣጫ መውረዱን ተናግረዋል።

በዞኑ በያዝነው የመኸር ምርት ዘመን 20 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ  ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም