ቀጥታ፡

አዋሽና ትሩፋቱ

አዋሽ ሀገሩን ተሻግሮ ላያልፍ መሃላ የፈፀመ ይመስላል። አዋሽ ሀገር ወዳድ፣ የሀገር ቤት ወንዝ፣ አልሚ እና ጠቃሚ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የአዋሽ ወንዝ ለኢትዮጵያ ከውሃ ሀብት እስከ መስኖ ግብርና፣ ከኢንዱስትሪ እስከ አረንጓዴ ልማት የሚያገለግል የሀገር ባለውለታ ነው።

አዋሽ የግብርና ምርት ማሳደጊያ፣ የኢንዱስትሪ መደገፊያ፣ የሰዎች ኑሮ መሠረትና የኢትዮጵያ የልማት አቅም ማሳያ መሆኑ ይታወቃል። በተለይም የዝናብ እጥረት ለሚገጥማቸው አካባቢዎች የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ የምግብ ምርትን ለማሳደግና የአካባቢውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ረገድ የማይተካ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።


 

 

በግምት 1 ሺህ250 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዋሽ ወንዝ የውሃ ሀብቱ በአንድ አካባቢ ብቻ የተገደበ አይደለም። ከከፍተኛ ቦታዎች እስከ ደረቅና ከፊል ደረቅ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በመዝለቅ ፈላጊዎቹን ያገለግላል። የውሃና የኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የአዋሽ ተፋሰስን ስፋት ወደ 110 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር፣ አማካይ ዓመታዊ የውሃ ምርቱን ደግሞ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያደርሰዋል። 


 

የአዋሽ ወንዝ በተለይም የአፋርና የተፋሰሱ ዝቅተኛ አካባቢዎች በመስኖ ለሰብል ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ለእንስሳት መኖ ምርት ያገለግላል። በወንዙ ተፋሰስ ከተገነቡት የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የወንጂ፣ የመተሃራ፣ የቀሰምና የተንዳሆ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች የግብርና ምርትን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ፣ በዓመት በተለያዩ ወቅቶች በማምረት ከችግርና ድህነት ለመውጣት እያገዙ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናዋን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት አዋሽ አለኝታነቱን አሳይቶ እየተሰራበት ነው። በተጨማሪም ለስኳር ልማት፣ ለጥጥ፣ ለአትክልትና ለፍራፍሬ ምርት የአዋሽ ውለታ ከፍተኛ ነው።

የአዋሽ ተፋሰስ ከግብርና ባሻገር ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እድገት ወሳኝ ስፍራ ነው። በተፋሰሱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ተቋማት፣ የማምረቻ ዘርፎች፣ የስኳር ፋብሪካዎችና የከተማ ልማት ስራዎች አቅርቦት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። እዎ እርግጥ ነው አዋሽ ውለታው ብዙ ነው፤ በታማኝነቱ የሚታወቅ ሀገር ወዳድ ወንዝ ነው።

የወንዙ ተጠቃሚዎችም የከተማ ነዋሪዎችና ገበሬዎች ብቻ አይደሉም። በተለይ በወንዙ የታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ለእንስሳት፣ ለግጦሽ መሬትና ለኑሯቸው መሰረት ሆኖ ዘመናትን እያገለገለ ይገኛል። በመሆኑም የአዋሽ ጉዳይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የአርብቶ አደሮች የኑሮ መሰረት ነው። ለተፈጥሮ ሃብትና ለዱር እንስሳት ጥበቃ፣ ለቱሪዝምና ለምርምር ጭምር አገልጋይ መሆኑንም መናገር ይቻላል።

የአዋሽ ወንዝ ትልቅ የልማት አቅም ቢኖረውም፣ ይህን ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም መፍትሔ የሚሹ ተግዳሮቶችም አልጠፉም። ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የከተማ ነዋሪዎችና አርብቶ አደሮች በተመሳሳይ የውሃ ሀብት ላይ ጥገኛ ስለሆኑ በድርቅ ወቅት የውሃ ክፍፍል ውስብስብ ይሆናል። ሌላው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥና የዝናብ መዛባት ሲከሰት የወንዙን ፍሰት ስለሚዛባ የድርቅና የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ የጎርፍ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ማጠናከር፣ የተፋሰስ ጥበቃ፣ የውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂና የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ስለመሆኑ ይመከራል።

የአዋሽ ወንዝን አቅም በሙሉ ለመጠቀም የሚያስፈልገው የውሃ ፕሮጀክቶችን መገንባት ብቻ አይደለም። የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች በብቃት ማስተዳደር፣ የውሃ ብክነትን መቀነስ፣ የመስኖ መሬቶችን በተሻለ ቴክኖሎጂ ማልማትና የወንዙን የተፈጥሮ ሥርዓት መጠበቅም ያስፈልጋል። በተመሳሳይ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ ለሚገኙ ማህበረሰቦችና ለተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር የሚያስፈልገው የውሃ መጠን መጠበቅ አለበት። የውሃ ሀብት ለአንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ መመራት ይገባዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም