ሀገርን በራስ የመከላከል አቅም ማሳደግ የሚያስችል መሰረት እየተጣለ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርን በራስ የመከላከል አቅም ማሳደግ የሚያስችል መሰረት እየተጣለ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2019 (ኢዜአ)፦ አስተማማኝና ኩሩ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገርን በራስ የመከላከል አቅም የማሳደግ መሰረት እየተጣለ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶችን ከሩሲያ ተረክባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ከሩሲያ መረከቧን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሳሪያዎቹ ርክክብ በውሉ መሰረት እ.አ.አ በ2027 ይፈጸም የነበረ ቢሆንም፣ በህንድ በነበራቸው ቆይታ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት አስቀድሞ መረከብ መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር 12 የሱ-35 ተዋጊ ኤርክራፍቶች እንዲሁም 4 ባትሪዎች ያሏቸው የኤስ-400 የአየር መከላከያ ስርዓቶች ኢትዮጵያ መረከቧን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት በሰላሙ ጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅት ባለማድረጋቸው ምክንያት ችግር ሲፈጠር ለአደጋ ሲጋለጡ እንደሚታይ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ላለማስደፈር በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የተረከበቻቸው የሱ-35 ኤርክራፍቶች በዓለም ላይ ካሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ግንባር ቀደም መሆናቸውን ነው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
መሳሪያዎቹ ከአየር ወደ አየር እንዲሁም ከአየር ወደ ምድር ውጊያ የማካሄድ ከፍተኛ አቅም ያላቸውና በተግባር የተፈተኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጡ የክሩዝ ሚሳኤል ጥቃቶችን እስከ 200 ኪሎሜትር ርቀት ድረስ የመለየት (Detect) እና የማክሸፍ (Intercept) ብቃት እንዳላቸው አስረድተዋል።
ይህንን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ለሀገር ህልውና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል የነበሩት የሱ-30 እና የአሁኖቹ የሱ-35 ተዋጊ ጄቶች የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።
በተጨማሪም በቂ ዝግጅት ማድረግ ውጊያን እንደሚያስቀርና ጥቃት እንዳይቃጣ ማድረጊያ አቅም (Deterrence) እንደሆነ በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ በሰሃራ በታች ባለው አፍሪካ ይህንን ትልቅ አቅም በመገንባት የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል።
በአካባቢው የአየር የበላይነትን መያዝ አስፈላጊ መሆኑንና አቅሙ በድሮን ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ጭምር መገንባት እንዳለበት ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ከሩቅ አከባቢዎች የሚቃጡ ማንኛቸውንም ሙከራዎች አስቀድሞ ለመመከት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ግንባታ በቀጣይ አመታት ኢትዮጵያን ከአስቸጋሪ ሁኔታዎችና ካልተገባ የውጊያ ፍላጎት የሚያድናት እንደሆነና ቀደም ሲል ለህዝብና ለፓርላማ የተገባውን ቃል መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮንትራት ጊዜው ሳይደርስ መሳሪያዎቹ ቀድመው እንዲረከቡ ላደረጉት ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ የኢትዮጵያ የክሩዝ እና የባሊስቲክ ሚሳይል የመከላከል አቅም በእጅጉ እንደሚጎለብትም ገልጸዋል።
ይህንን አቅም በቀጣይነት በመገንባት የኮራች እና የጸናች ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት እንደሚጣል ተናግረዋል።
ሂደቱ ቀድሞ ከመናገር ይልቅ ሰርቶ ማሳየትን መሰረት ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለመላው የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና ለሀገር ወዳድ ዜጎች በሙሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።