የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ፍኖት፦ የአዲሱ ትውልድ የክህሎት ማበልጸጊያ መንገድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ፍኖት፦ የአዲሱ ትውልድ የክህሎት ማበልጸጊያ መንገድ
በሀሪ መልስ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም አቀፍ የበላይነትና የኢኮኖሚ ጥንካሬ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ አቅም እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያም ይህንን የዓለም አቀፍ እውነታ በመገንዘብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎትን ወደሚያሳልጥ የላቀ የዲጂታል ምዕራፍ ተሸጋግራለች። በዚህ ሀገራዊ የሽግግር ጉዞ ውስጥ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የጀማሪ ፈጠራ ስራ (Startups) የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዋና ሞተር በመሆን ግንባር ቀደም ስፍራ እየያዙ ነው።
በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደትም በቴክኖሎጂ ስነ-ምህዳር ውስጥ አዲስ የስራ ባህልና የፈጠራ ምህዳር ፈጥሯል። የፖሊሲ ስትራቴጂዎች፣ የሕግ ማዕቀፎችና የመሰረተ ልማት አውታሮች ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል የማድረግ ታላቅ ተስፋን የሰነቁ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አፈጻጸም የቀመረችውን ልምድና ተሞክሮ ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በማሸጋገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ወደ ላቀ ደረጃ የሚሸጋግር ትልቅ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች። የስትራቴጂው መሰረታዊ ዋና ዓላማም የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል አማራጭ ማቅረብ፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ማድረግ እና የፋይናንስ አካታችነትን ማረጋገጥ ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የታለመለትን ግብ አሳክቷል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም የኢትዮጵያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ በስኬታማ የትግበራ ምዕራፍ እየተጓዘ ይገኛል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ተደራሽነትን በማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል በመፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን በማጎልበት ቁልፍና መሰረታዊ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል። እነዚህ ትልሞችም የሕዝብ ዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋት ላይ ትልቅ ስፍራ እየተሰጣቸው መጥቷል። ይህም ሰው ተኮር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ምኅዳር በመፍጠር የዜጎችን ኑሮ ወደ ትልቅ አቅም እያስፈነጠረ ይገኛል። በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ፍኖተ ካርታ የሚከናወኑ ሥራዎችም የመደመር መንግሥት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስኬቶችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ያመላክታል።
«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የታለመለትን ግብ አሳክቶ ተጠናቋል። በዛሬው ዕለትም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በይፋ አስጀምረናል። ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት የስትራቴጂው ቁልፍ መሠረታዊ ትልሞች ናቸው። እነዚህ ትልሞች እንዲሳኩም በተለይ የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋት ላይ ትልቅ ሥራ የሚከናወን ሲሆን ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም ይፈጥራል። በአጠቃላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ሥራዎች የመደመር መንግሥት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ ናቸው።» — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትም በተለያዩ የግብይትና የመተግበሪያ አማራጮች እየተሳለጠ ነው። የቴሌብርና የኦንላይን የክፍያ ሥርዓቶችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኙ ነው። አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም ያለ ማስያዣ ብድር በማግኘት የልማት ስራዎቻቸውን ወደ ላቀ የዕድገት ምኅዳር የሚያስፈነጥሩበትን አዲስ ዕድል ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ ማዕከላት ግንባታና የክላውድ ኮምፒውቲንግ መሰረተ ልማት ዝርጋታም የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን የሚመጥን አቅም ገንብቷል። የኢንተርኔት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባርም የመረጃ ሉዓላዊነትና የሳይበር ደህንነትን የማረጋገጥ አካል ናቸው። እነዚህም የኢትዮጵያን ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማትና የመረጃዎች ደህንነትን እንዲጠበቁ እያስቻለ ነው።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው በአፍሪካ የመጀመሪያው ሁሉን አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲና ስትራቴጂም ታሪካዊ እርምጃ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂም በቴክኖሎጂ ዘርፍ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ስልጡን የሰው ሃይል በመገንባትና የመረጃ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ለስታርትአፖች ምቹ የፈጠራ ማዕቀፍ መፍጠር አስችሏል።
«በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያየሁት ነገር፤ ሰው የጠራ ርዕይ ካለው፣ በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሚሰራ ከሆነ አንድን ነገር ባየው ልክ ማሳካት እንደሚችል፤ ኢትዮጵያ ብቃት ያላት ሀገር እንደሆነች ነው።» — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የምርምር፣ ልማትና የፖሊሲ አፈጻጸም ዋና መሪ አካል ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ይህም የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶችና ዜጎች ክህሎታቸውን በማበልጸግ ወደ ተግባር የሚገልጡበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል። የአዲስ አበባ የቦሌ አትላስ ኮሪደር የንግድ ጀማሪ ፈጠራ ስራ (Startups)፣ የኢትዮጵያ አይሲቲ ቪሌጅ ሮቦቲክስና ከፍተኛ ምርምር፤ የፈጠራ ማዕከላት የኢትዮጵያ ተስፋ ወደ ተጨባጭ ተግባር እየተቀየረ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው።
ይህም በግብርና ዘርፍ የሰብል በሽታን በምስል በመለየት፣ በጤና የሕክምና ምስሎችን በመተንተን እና በፋይናንስ ዘርፍ ደግሞ በርካታ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መፍትሔን መተግበር የሚያስችል ዕድል መፈጠሩን ያመላክታል።
ኢትዮጵያ የመደመር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲን በማቋቋም አህጉራዊ የዲጂታል ልማት ማዕከል የሚያደርጋትን ወሳኝ መንገድ ተልማለች። ዩኒቨርሲቲውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙሉ በሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና በላቁ የኮምፒውቲንግ ሳይንሶች ብቻ ከተመደቡ ጥቂት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የሚመደብ ነው። ሥርዓተ-ትምህርቱ ከወረቀት ላይ ትምህርት ይልቅ በተግባራዊ አፕሊኬሽኖች፣ በማሽን ለርኒንግ፣ በሮቦቲክስ፣ በዳታ ማይኒንግ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ምርምር ላይ ያተኮረ ይሆናል።
በኢትዮጵያ የሚሰሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መፍትሔዎች ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ከነዚህም መካከል በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ እና ሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የትርጉም፣ የድምፅና የጽሑፍ ማቀናበሪያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መሳሪያዎች ይገኙበታል። እነዚህ በሀገር በቀል ድርጅቶች የሚለሙ የቴክኖሎጂ አማራጮችም ከዓለም አቀፍ አፕሊኬሽኖች የተሻለ የቋንቋ ትክክለኛነት በማረጋገጥ ላይ ናቸው።
የአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ስልጠና ተነሳሽነትም በሶስት ዓመታት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ አናሊቲክስ፣ በአንድሮይድ ዴቨሎፕመንት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መሰረታዊ ክህሎት እንዲጨብጡ አድርጓል። ተነሳሽነቱም የዲጂታል ፈጠራና ምርምርን በማጎልበት የቴክኖሎጂ ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን ማፍራት እያስቻለ ነው።
የስታርትአፕ አዋጅ (Startup Proclamation No. 1396/2025) መጽደቁ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል። የአሰራር ሥርዓቱም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ስታርትአፖችና የሥነ-ምህዳር ደጋፊዎች በአንድ ቦታ እንዲመዘገቡና ሕጋዊ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ያስችላል። አዋጁም የስታርትአፕ ግራንት (Grants)፣ የብሔራዊ ክሬዲት ጋራንቲ ፈንድ (Credit Guarantee Fund) እና የገንዘብ ፈንድ (Fund of Funds) አሰራሮች በመዘርጋት የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ዝንባሌን ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የስታርትአፕ ስነ-ምህዳር እርስ በእርስ የተቀናጁና አንዱ ለሌላው ማፋጠኛ መሳሪያነት የተዋቀሩ ናቸው። የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ለAI ሞዴሎች ስልጠና አስፈላጊውን የኮምፒውቲንግ አቅም ያቀርባሉ። የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎች ለስታርትአፖች አዲስ ምርትና አገልግሎት ፈጥረው ለገበያ እንዲያቀርቡ መንገድ እየከፈቱ ነው። ስታርትአፖች ደግሞ የፈጠሯቸው የዲጂታል አገልግሎቶች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦችን በማሳለጥ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከፖሊሲ ቀረፃ ወደ ተጨባጭ የልማት ስነ-ምህዳር ግንባታ ሽግግር በአፍሪካ ደረጃ የቴክኖሎጂ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ማዕከል የማድረግ ታላቅ ዕድል ከፍቷል። ይህ ታላቅ ርዕይ ሙሉ በሙሉ እውን እንዲሆንም የፖሊሲ ማዕቀፎችን፣ የተቋማት ጥረትን እና የወጣቶችን የፈጠራ አቅም በተቀናጀ መልኩ ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ይህንን ዘላቂ ስኬት ለማረጋገጥም ስትራቴጂክ ትልሞችን በተቀመጠላቸው መርሃ ግብር መተግበር ወሳኝ ነው። የቴሌኮም፣ የብሮድባንድና የዳታ ማዕከላት ተደራሽነትን በማስፋፋት ለሀገር ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አልሚዎች እና ስታርትአፖች በዝቅተኛ ወጪ የሚጠቀሙበት ምቹ የመሰረተ-ልማት ምህዳር መፍጠር ያስፈልጋል። በጸደቀው የስታርትአፕ አዋጅ የተመላከቱትን የብሔራዊ ክሬዲት ጋራንቲ ፈንድ እና የገንዘብ ፈንድ አሰራሮችን በመተግበርና የቬንቸር ካፒታል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታት የጀማሪ ስራዎችን የፋይናንስ እጥረት መቅረፍ ይገባል።
በተጨማሪም፣ ከአምስት ሚሊዮን ኮደርስ እና ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ሰልጣኞችን በቀጥታ ወደ ስራ የሚቀይሩ የኢንኩቤሽን ማዕከላትን ማብዛትና በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ የSTEM ክህሎቶችን ማጠናከር ወሳኝ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች፣ በምርምር ተቋማት እና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ያለውን ቅንጅት በማጠናከር የመንግስት ተቋማት የሀገር ውስጥ ስታርትአፖች ምርቶችን ቅድሚያ ሰጥተው እንዲገዙ ማበረታታት፣ የመረጃ ሉዓላዊነትን፣ የሳይበር ደህንነትን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ስነ-ምግባር ደንቦችን በጥብቅ ማስከበር ያስፈልጋል።